ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሥነ ምድርና የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን ለመቀነስ የግብርና ስራዎችንና የአኗኗር ዘይቤን ማጤን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሥነ ምድርና የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን ለመቀነስ የግብርና ስራዎችንና የአኗኗር ዘይቤን ማጤን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መሰንጠቅ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ ሱናሚ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎችም የተፈጥሮ ክስተቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ዓለም የሚያስተናግዳቸው የተፈጥሮ ክስተቶች ናቸው።

በኢትዮጵያም ለመሬት መንቀጥቀጥና መሰንጠቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው የሚታወቁ ቢሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች በብዛት የሚከሰተው ግን የመሬት መንሸራተት አደጋ ነው፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ፤ የመሬት መንሸራተት አደጋ በተፈጥሯዊ ገፊ ምክንያቶች በተለያዩ የዓለም አገራት የሚከሰት መሆኑን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የመሬት መንሸራተት አደጋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰት መሆኑን ገልጸዋል።

የአለቱ አወቃቀር፣ የመሬቱ አቀማመጥ፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤና ሌሎችም የመሬት መንሸራተት ክስተትን የሚወስኑ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውንም ዘርዝረዋል።

በመሆኑም የመሬት መንሸራተት አደጋ ገፊ ምክንያቶችን በመረዳት የመከሰት እድሉን መቀነስ፣ ጊዜውን ማራዘም ወይም የሚያደርስውን ጉዳት መቀነስ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚሁን ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ ቢቻልም የመሬት መንሸራተትን በፍፁም ማስቀረት ግን የማይቻል መሆኑን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ለመሬት መንሸራተት አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉ አካባቢዎች በጥናት የተለዩ መሆኑን ጠቅሰው ለአደጋዎቹ መከሰት የሰዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

በተፈጥሯዊ አቀማመጡ የተዳፋታማ መሬት የደን ጭፍጨፋ፣ የተራራ ላይ እርሻ እና ሌሎችም ማህበረሰባዊ ክዋኔዎች ለመሬት መንሸራተት ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደ ገፊ ምክንቶቹ ነባራዊ ሁኔታ በፍጥነት ወይም በረጅም ጊዜ ሂደት ሊከሰቱ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አደጋዎችን ለመቀነስ በትብብር መሥራት ይገባለ ብለዋል፡፡

በመንግስት እየተደረገ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም የመሬት መንሸራተትን ታሳቢ ያደረገ የግብርናና የአኗኗር ዘይቤ መከተል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የሥነ ምድር አደጋዎችን ለመቀነስና የመሬት መንሸራተት አደጋን ለመከላከል የግብርና ስራን እና የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤን ማጤን ይገባል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ከመሬት የተለየ ድምጽ ከተሰማ፣ ዛፎች፣ የውሃና የመብራት ፖሎች የመንጋደድ ምልክት ካሳዩ የመሬት መንሸራተት አደጋ መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ መረጃውን ማድረስና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም