በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የቴሌኮም ኢንቨስትመንት ከባቢና የመንግሥት ድጋፎች ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎታል- ዊም ቫንሄሊፑት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የቴሌኮም ኢንቨስትመንት ከባቢና የመንግሥት ድጋፎች ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎታል- ዊም ቫንሄሊፑት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የቴሌኮም ኢንቨስትመንት ከባቢና የመንግሥት ድጋፎች ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ማስቻሉን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄሊፑት ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለኃብቶች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄሊፑት ኩባንያው በአንድ ሺህ የቴሌኮም ታወር ሥራ መጀመሩን አስታውሰው አሁን ላይ በራሱ አቅም የገነባው ሦስት ሺህ ታወር እንዳለው ተናግረዋል።
ኩባንያው ስራ ከጀመረ አንስቶ በ26 የኢትዮጵያ ዋናና 500 አነስተኛ ከተሞች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ ከተሞች ለሚገኙ 50 በመቶ ለሚሆኑ ደንበኞቹ የ4ኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት ገልጸው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደንበኞቹን ከ10 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኩባንያው ኤምፔሳ በተሰኘ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያው ተጨማሪ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በመተግበሪያው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ መፈጸም መጀመሩን በማንሳት በቀጣይ የነዳጅ፣ የታክስና ሌሎች ክፍያዎችን ጨምሮ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኩባንያው አሁን ላይ ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የቴሌ-ኮም የኢንቨስትመንት ከባቢና መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ድጋፍና ክትትል ለተጠቀሱት ስኬቶች መመዝገብ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።
በቀጣይ ዓመታት መሰረተ ልማት በማስፋፋትና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ለዲጂታል ኢትዮጵያ መሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ በበኩላቸው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሽፋን እንዲሰጥ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።