በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 40 በመቶው ችግኞች የሚተከሉት በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 40 በመቶው ችግኞች የሚተከሉት በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 በመቶው ችግኞች የሚተከሉት በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የድሬደዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች በድሬዳዋ አሊ ቢራ ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች በጂኦ ሪፈረንስ የሚታወቁ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ የተፋሰሶችን ደህንነት ለመጠበቅ አጠቃላይ ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 40 በመቶው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሬዳዋ በምትገኝበት የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚከናወን የችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ እንዲሁም በእውቁ የጥበብ ሰው አሊ ቢራ መታሰቢያ ፓርክ ችግኝ በመትከላችን አስደስቶናል ሲሉም ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ የአረንጓዴ አሻራ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በድሬዳዋ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የአፈር መሸርሸር ድርቅና የጎርፍ ተጋላጭነትን መቀነስ ተችሏልም ብለዋል።
ዘንድሮ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና የተስተካከለ የአየር ሁኔታን የሚፈጥሩ 3 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገለጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋቶችን ለማፅናትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።