በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብርና ማቀነባበሪያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል - የፋኦ ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ማክሲሞ ቶሬሮ - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብርና ማቀነባበሪያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል - የፋኦ ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ማክሲሞ ቶሬሮ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብርና ማቀነባበሪያ የኢንቨስትመንት መስክ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ማክሲሞ ቶሬሮ ገለጹ።
ዶክተር ማክሲሞ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሐ ይታገሱ (ዶ/ር) እና በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ጋር በመሆን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርት ሂደትን ተመልክተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙትን ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ የቢራ ብቅል አምራችና ሺንትስ የተሰኘ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተለይም በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ለመረዳት መቻላቸውን ዶክተር ማክሲሞ ገልጸዋል።
ይህም ለኢንቨስትመንት ፍሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መናገራቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የፔሩ ዜግነት ያላቸው የፋኦ ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ማክሲሞ ቶሬሮ ትናንት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መወያየታቸው የሚታወስ ነው።