ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አጀንዳ የማሰባሰብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ 

ድሬዳዋ ፤ነሐሴ 8/2016 (ኢዜአ)፡-የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠርና የከተማ ማህበረሰብ ወኪሎች ላለፉት ሦስት ቀናት ሲያካሂዱት የነበረው ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ላይ የተሳተፉት አስቀድመው ለአጀንዳ ልየታ ከአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የማህበረሰብ ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮች ናቸው።

የኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታና ምክክር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  በአሥር ምድብ ተከፍለው የመጀመሪያ ምዕራፍ የአጀንዳ ልየታ ላይ የተሳተፉት 500 የሚጠጉ ወኪሎች ለሀገራዊው ምክክር ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች አሰባስበው አጠናቀዋል።


 

ወኪሎች ከአጀንዳ ማሰባሰብ ባሻገር ለቀጣዩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የሚመካከሩ 60 ወኪሎችን ከ10 ዋና ዋና ቡድኖች መምረጣቸውን አስታውቀዋል።

ላለፉት ሦስት ቀናት ያሰባሰቧቸውን አጀንዳዎችንም ለመረጧቸው 60 ወኪሎች ማስረከባቸውን ነው አቶ ተመስገን የተናገሩት።

እነዚህ የተመረጡ ወኪሎች በቀጣዮቹ ቀናት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ  ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም