በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመቀመር የኮሪደር ልማት ለማከናወን ዝግጅት ማድረጉን የጦራ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማከናወን በመንግሥት ግብ ይዞ እየተሰራ ይገኛል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ በአስደናቂ ውጤት ተመዝግቦበታል።
በመዲናዋ በፍጥነትና በጥራት የተከናወነው ሥራ በኮሪደር ልማት ጥሩ ማሳያ ተደርጎ በሌሎች የክልል ከተሞችም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የተመረጡ 30 ከተሞች የየራሳቸውን ዕቅድና ማስተግበሪያ ስልቶች ቀይሰው የኮሪደር ልማቱን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ካሉ ከተሞች መካከልም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ጦራ ከተማ ትጠቀሳለች።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጦራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሁሴን ሱናሞ፤ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመቀመር ለኮሪደር ልማት ሥራው ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።
ለኮሪደር ልማቱ ክንውን የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የግዥና አቅርቦት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመብራት ተከላና ተያያዥ ልማቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ገልፀዋል።
ከአረንጓዴ ልማትና የውበት ሥራዎች ጋር በተገናኘም ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ የ5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ለመጀመርም በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ከንቲባው፤ ከተማ አስተዳደሩ በልማቱ ምክንያት ለሚነሱት ምትክ ቦታና ተገቢ የሆነ ካሳ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በጦራ ከተማ የሕዝቡ የመልማት ፍላጎትና ተሳትፎ ማደጉን ያነሱት ከንቲባው፤ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በ20 ሚሊየን ብር የጤና ተቋም እንዲሁም የፖሊስ ማዕከላት ግንባታ መከናወኑን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩን ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች የዲጂታል አገልግሎትን እውን ለማድረግ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።