ለዝናብ አጠር አካባቢ ተስማሚ የሆነ የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም መጀመራችን ከአካባቢያችን ፀጋ ተጠቃሚ አድርጎናል - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለዝናብ አጠር አካባቢ ተስማሚ የሆነ የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም መጀመራችን ከአካባቢያችን ፀጋ ተጠቃሚ አድርጎናል - አርሶ አደሮች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016 (ኢዜአ)፦ ለዝናብ አጠር አካባቢ ተስማሚ የሆነ የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም መጀመራችን ከአካባቢያችን ፀጋ እንድንጠቀም አድርጎናል ሲሉ የምስራቅ ቦረና የጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትራክተር ማረስ መጀመራቸው፣ ዘመናዊ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት መጠቀማቸውና የደረሰ ሰብላቸውን በኮምባይነር መሰብሰብ መቻላቸው ምርታማ አድርጓቸዋል፡፡
በጉጂ ዞን የአዶላ ረዴዴ ወረዳ አርሶ አደር ሶፊ ደንዳኡ ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ ሰብልና አትክልት ማልማት ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት መቆጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በባህላዊ መንገድ ዝናብ ጠብቀው በሚያርሱበት ወቅት ህይወታቸው አስቸጋሪ ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር ተናግረዋል።
በባህላዊ አስተራረስ በሄክታር ከ10 ኩንታል የማይበልጥ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ በኩታ ገጠም ማረስ ከጀመሩ በኋላ በሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአንድ የምርት ወቅት ከበቆሎ ሽያጭ ከ300 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ጠቅሰው፤ ገቢያቸውን በመቆጠብ በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ሸህ ጠሃ በሸር እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ከከብት እርባታ ውጭ በሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች ላይ ግንዛቤ ስላልነበራቸው የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በግብርና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ከቀበሌው አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር በመደራጀት በሜካናይዜሽን እርሻ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ባመጡት ለውጥ ከዕርዳታ ጠባቂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገራቸውን በስኬት አንስተዋል፡፡
ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በመጠቀም ውጤታማ መሆን መቻላችን በቀጣይ በበለጠ ሁኔታ ድጋፍ ለማግኘትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያስችለናል ብለዋል፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያው አቶ ናስር ሲራጅ በበኩላቸው ዞኑ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ ሰፊ ለም መሬትና አየር ንብረት ቢኖረውም የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘመናት በእንስሳት እርባታ ብቻ ይተዳደሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይህም ድርቅ በተከሰተና የዝናብ እጥረት ባጋጠመ ቁጥር ለአስከፊ ችግር ሲዳርጋቸው መቆየቱን አስታውሰው መንግስት ባደረገው የሙያና የተቀናጀ ሜካናይዜሽን ድጋፍ የዞኑ ማህበረሰብ ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት መቀየሩን ገልጸዋል፡፡
የዞኑ ነዋሪዎች አሁን ላይ በኩታ ገጠም እርሻ ምርት ከማምረት አልፈው ወደ ተጠቃሚነት መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘር ወቅት በመሆኑ፤ ማህበረሰቡ ከገበያ አኳያ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አስረድተዋል፡፡