ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016 (ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩት የህንድ ባለሃብት ብሃቬሽ ቻንዳሪ ገለጹ።

በብረት ምርት ላይ የተሰማሩት ብሃቬሽ ቻንዳሪ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ገቢራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እድገትን በማስቀጠል ውስንነት ነበረበት።  

ይህንንም ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ገቢራዊ ማድረጉን  ጠቅሰው፤ ማሻሻያው ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የአገሪቱን እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚበረታታ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል።   

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም ሥር የሰደዱ የመዋቅራዊ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለአብነትም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት በመፍታት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠልና የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሠረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።   

ይህም ብቻ ሳይሆን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሁሉን አቀፍና የቢዝነስ ትብብር ከባቢን የሚያጎለብት በመሆኑ ሊደገፍ ይገባል ሰሉም ነው የተናገሩት።  

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ኢኮኖሚውን ለውድድር ክፍት በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመሠረታዊነት የሚለውጥ እርምጃ መሆኑንም ጠቅሰዋል።  

በኢትዮጵያ ውስጥ ሸማቹ ማኅበረሰብ አማራጮችን ባለማግኘቱ እየተቸገረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ይህንን ሊቀርፍ የሚችል የአምራች ዘርፉን የሚያበረታታና ገበያውን የሚያሰፋ አማራጭ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል። 

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማስፋት ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ መሰል እርምጃዎች ሸማቹ ላይ ጫና የሚያሳድሩ በተለይም በጥቂት የገበያ ተዋንያን የሚደረጉ ቁጥጥሮችን በማስወገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።   

መንግሥት የማሻሻያ ፖሊሲውን ገቢራዊ ከማድረጉ በፊት የቤት ኪራይን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረትና ሌሎች ዝግጅቶች የሚደነቁ መሆኑን ጠቅሰው አነዚህም በተለይም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ እርምጃ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ይህም በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች አስቀድሞ ለይቶ መፍትሔ የሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በየትኛውም የሕይወት ጎዳና ላይ የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ይህ የማሻሻያ ፖሊሲ አዎንታዊ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ በማመን ለተግባራዊነቱ እንዲተጉም ጠይቀዋል። 

የማሻሻያ ፖሊሲው ተተግብሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሁሉም ዜጋ እንዲሁም የተቋማት ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም