ቀጥታ፡

የአሶሳ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ52 ሚሊዮን ብር የምግብ ዘይት ፋብሪካ ማስፋፊያ እያካሄደ ነው

አሶሳ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ52 ሚሊዮን ብር የምግብ ዘይት ፋብሪካ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ቸኮል ለኢዜአ እንደገለፁት የአሶሳ እና አካባቢው አርሶ አደሮች የምግብ ዘይት ፋብሪካ በ2003 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፡፡

በአሁኑ ወቅት በቀን የሚያመርተውን ከሁለት ሺህ በላይ ሊትር የኑግ ዘይት ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡


 

ዩኒየኑ በከተማው ከሚገኙ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች የዘይት ዋጋ በሊትር የ50 ብር ቅናሽ እያቀረበ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

እየጨመረ የመጣውን የከተማው ህብረተሰብ የዘይት ፍላጎት ለማርካት በ52 ሚሊዮን ብር ፋብሪካውን የማስፋፋት ስራ መጀመሩን ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በገባው ውል መሰረት በቅርቡ የፋብሪካውን ማሽኖች ግዢ እያካሄደ እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ እሸቱ፤ ሌሎችም ለማስፋፊያ ስራው ግብዓቶች በቅርቡ እንደሚሟሉ አስረድተዋል፡፡

በሚቀጥሉት አራት ወራት የማስፋፊያውን ግንባታ አጠናቆ ማምረት ሲጀምር በቀን ወደ ስድስት ሺህ ሊትር እንደሚያድግ ገልጸዋል፡፡

ማስፋፊያው የዩኒየኑ አባላት ከሆኑ አርሶ አደሮች በመረከብ ከሚያመርተው የኑግ ዘይት በተጨማሪ የሰሊጥ፣ የለውዝ፣ የአኩሪ አተር እና የሱፍ ዘይቶችን ማምረት እንደሚያስችለውም ነው ያስረዱት፡፡

ይህም አሁን ያሉትን 50 የፋብሪካው ሠራተኞችን ቁጥር ወደ 100 እንደሚያደርስም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ዩኒየኑ ከክልሉ መንግስት ለቅባት ሰብሎች ማምረቻ የሚውል 200 ሄክታር የእርሻ መሬት መረከቡንም አቶ እሸቱ አመልክተዋል፡፡


 

የፋብሪካው ዘይት ምርት ተጠቃሚ ከሆኑት የአሶሳ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ባዩሽ ጥላሁን በሰጡት አስተያየት፤  በከተማው በ1 ሺህ 200 ብር የሚሸጠውን ዘይት ከፋብሪካ በ1 ሺህ 70 ብር እየሸመቱ ነው፡፡

ወይዘሮ በላይነሽ ያየህይራድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የዩኒየኑ የዘይት አቅርቦት በተለይም በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማው ነዋሪዎችን እየደገፈ ነው ብለዋል፡፡ 

በ65 መሠረታዊ ማህበራት የተደራጀው የአሶሳ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡

ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳለውም ታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም