በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተያዘ ሰው የለም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተያዘ ሰው የለም
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተያዘ ሰው አለመኖሩን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ዛሬ የአፍሪካ ሲዲሲ ባወጣው መግለጫ፣ በ13 የአፍሪካ ሀገራት፣ 2,863 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸው እና፤ 517 ለህልፈት መዳረጋቸዉ መረጋገጡን ጠቅሶ በሽታው የህብረተሰብ ጤና አህጉራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑም ተገልጿል።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የጋራ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑም ተጠቁሟል።
በአገራችን ኢትዮጵያ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና ሞያሌን ጨምሮ ሌሎች የመግቢያ ቦታ ላይ የቁጥጥርና ማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑንና ጉዳዩን ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተሉት መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
እስካሁን በሀገራችን ምንም አይነት በበሽታው የተያዘ ሰው አለመገኘቱንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋና ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት መሆናቸውም ተጠቅሷል።
እነዚህ ምልክቶች መከሰታቸው የተረጋገጠ እና በቅርቡ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው ሀገሮች የጉዞ ታሪክ ያለው ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበትም ተጠቁሟል።
በሽታው በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን በመግቢያና መውጫ ኬላዎች አካባቢ የሕብረተሰቡን ተሳትፎን በማሳደግ የተጠናከረ የቁጥጥርና መከላከል ስራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ ወይም በ952 እና 8335 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረግ የሚቻል መሆኑንም ገልጾ፤ ሁሉም አካላት ሊከተሏቸው የሚገቡ ሂደቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስመልክቶ በቅርቡ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥም ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣም መረጃ አመላክቷል።