ቀጥታ፡

ለድንገተኛ አደጋዎች የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ ነው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በዓለም ላይ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሥርዓት ባልተመሩባቸው አጋጣሚዎች በሰዎች ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሰዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም አገራት የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ግጭትና መሰል አደጋዎች ቀውስ በመፍጠር የሰዎችን ህልውና አደጋ ላይ ሲጥሉ ይታያል።

በመሆኑም የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን እቅድ ያዘጋጁ አገራት አደጋውን መቀነስ ሲችሉ፤ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ያልቻሉት ደግሞ ለከፋ ችግር ሲዳረጉ ይስተዋላል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ ከዚህ ቀደም ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ማን በምን መልኩ መረጃ መስጠት እንዳለበት የሚያመላክት ግልፅ አሰራር እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ የቀውስ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር አደጋ ሲያጋጥም ከችግሩ በፍጥነት ለመውጣት በቅድሚያ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እየተዘጋጀ ያለው የቀውስ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ማኑዋል አደጋዎች ሲከሰቱ ከመበየን ጀምሮ ከፌደራል ጀምሮ እስከታች ባሉት መዋቅሮች የሚኖረውን ሀላፊነት በግልጽ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲም እያዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማንዋል አንዱ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንዋሉ አደጋውን ለመቀልበስ ማን በምን ጉዳይ ላይ መረጃ መስጠት እንዳለበት ግልጽ ማብራሪያ የተቀመጠበት መሆኑንም አብራርተዋል። 

የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማንዋሉ ወጥ በሆነ ሀገራዊ ይዘት እየዘጋጀ ሲሆን፤ ክልሎችና ተቋማት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የራሳቸውን ሰነድ ያዘጋጃሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም