ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ስራ  ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ ነው  

ሐረር ፤ ነሐሴ 08/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ የሚገኘው ስራ  ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተና ተስፋ ሰጪ መሆኑን  በሐረሪ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል የጀመረው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደቀጠለ ነው።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ ያገኘናቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንደተናገሩት፤ የሀገራዊ ምክክሩ እያከናወነ የሚገኘው ስራ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ እና ተስፋ ሰጪ ነው።


 

የመላው ኢትዮዽያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሐረሪ ክልል ሰብሳቢ  አቶ ተስፋ ሚልኬ  የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታ፣ የህብረተሰብ ተወካዮች መረጣ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብና ሌሎች ሂደቶችን በጠበቀ መልኩ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ በመሆኑ ምክክሩ ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከራስ  ፍላጎትና ከራስ አስተሳሰብ በዘለለ መልኩ "ኢትዮጵያ ምን ያስፈልጋታል? ህዝቡስ ምን ይፈልጋል?" በሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባና በዚህ ላይ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሐረር ሊቀ  መንበር አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በሀገሪቷ የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች አገርን ለማስረከብ  የምክክር ኮምሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ስራ አበረታች ነው።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለአገር ልማት፣ እድገትና ሰላም የሚበጁትንና እየተከናወኑ ያሉትን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው፤በሌላ በኩል ደግሞ ያልተስተካከለውን በምክክሩ ሃሳብ በመስጠት እንዲስተካከል ማድረግ አብሮ መስራትን ማጎልበት አስውፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም የፓርቲውን ሃሳቦች እያንጸባረቁ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ የኢዜማ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሪት ማህሌት ዘውዱ በበኩላቸው፤ "ምክክሩ ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት እንድንችል የሚያሸጋግር ድልድይ ነው፤ በዚህም ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ስራም ተስፋ ሰጪ ነው" ብለዋል።


 

በተለይም ምክክሩ ችግሮችንንና አለመግባባቶችን ለመፍታት መፍትሄ  የሚሰጥና ለአገር ልማትና ሰላም አስተዋጽዎ የሚያበረክት መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ላይ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ብልጽግናን የወከሉት አቶ ሀሰን አብዲ በበኩላቸው፤ "ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ የተሻለ ለማድረግና  ሁሉንም የሚያግባባና የተሻለች  አገር ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳው የጎላ ነው ስራውም ተስፋ ሰጪ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።


 

በተለይ በምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈና ሃሳቦች በነጻነት የሚቀርቡበትና በዴሞክራሲያዊ መንገድና ሀገርን የሚያሻግር  ውይይት እየተካሄደበት የሚገኝ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ባለፉት ሦስት ቀናት የወረዳ ተወካዮችን በማወያየት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ሁለተኛ ዙር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያከናወነ ይገኛል። 

በክልሉ እየተካሄደ በሚገኘው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የመንግስት አካላት እንዲሁም የማህበራትና ተቋማት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም