ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃደኞች ቤታችን መታደሱ ሕይወታችንን ከማለምለም ባለፈ አስታዋሽ አለን ብለን እንድናስብ አድርጎናል--ተጠቃሚዎች

ዲላ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በበጎ ፍቃደኞች መኖሪያ ቤታችን መታደሱ ሕይወታችንን ከማለምለም ባለፈ አስታዋሽ አለን ብለን እንድናስብ አድርጎናል ሲሉ በጌዴኦ ዞን ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት ግንባታ ዘመቻ ከ1ሺህ 800 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።


 

ተጠቃሚዎች እንዳሉት በበጎ ፈቃደኞች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የነበረባቸውን ችግር የሚፈታ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የዲላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ረጋሳ እንዳሉት፣ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር ለጭንቀት ይዳረጉ ነበር።


 

ደሳሳ ጎጇቸው በተለይ በክረምት ወራት ዝናብና ብርድ እያስገባ እሳቸውንና ልጆቻቸውን ለበሽታ በማጋለጥ በኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰዋል።

የዘንድሮው ክረምት እንዳለፉት ዓመታት ክረምቶች ለችግር ያጋለጣቸው ሳይሆን ደስታን እንዳመጣላቸው ነው የተናገሩት።

በበጎ ፈቃደኞች የመኖሪያ ቤታቸው በአዲስ መልክ ለመስራት ግንባታ መጀመራቸው በህይወታቸው ብሩህ ተስፋ እንዲታያቸው ማድረጉንና ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ቡሌ ወረዳ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተጀመረው የቤት ግንባታና እድሳት ሥራ የቀጣይ ህይወታቸውን እንዳለመለመው የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ ውድነሽ አታራ ናቸው።


 

በአቅም ውስንነት ምክንያት ሊፈርስ በደረሰ ቤታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ህይወታቸውን ሲመሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በተለይ በክረምት ወቅት በዝናብና ብርድ በተደጋጋሚ ለጤና ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃደኞች መኖሪያ ቤታቸው ተሻሽሎ እየተገነባላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

"ያረጀ ቤቴ ፈርሶ በአዲስ የግንባታ ሥራ መጀመሩ ኑሮዬን ያሻሽለዋል" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ብርቱኳን ዋቆ ናቸው።

የቤታቸው መገንባት በተለይ ተማሪ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ መሰረት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በጌዴኦ ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3ሺህ 500 በላይ ቤቶች ግንባታና ጥገና ሥራ ለማከናወን ታቅዱ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደግነት ሃይሉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች በዘመቻ የተጀመረው ከ1ሺህ 800 በላይ ቤቶች ግንባታና ጥገና ሥራ የዚህ አካል መሆኑንም አስረድተዋል።

ግንባታውን በተያዘው ወር አጠናቆ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘመቻ የተጀመረው የቤት ግንባታና አድሳት ሥራ ከ8ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።


 

ህብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባርን ወቅት ጠብቆ የሚያከናውነው ብቻ ሳይሆን የሁሌም ተግባሩ እንዲያደርገው እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማገዝ ባለፈ እርስ በእርስ የመደጋገፍ እሴትን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም