ችግሮችን በመመካከር እና በመደማመጥ መፍትሄ በመስጠት በአንድነት የተሻለች አገር መገንባት እንችላለን - በድሬዳዋ የውይይቱ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በመመካከር እና በመደማመጥ መፍትሄ በመስጠት በአንድነት የተሻለች አገር መገንባት እንችላለን - በድሬዳዋ የውይይቱ ተሳታፊዎች
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ በመመካከር እና በመደማመጥ የአገርን ዘላቂ ሰላም እና ጥቅሞች በማስጠበቅ የተሻለች አገር ለትውልድ የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በትጋት እንደሚወጡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የድሬዳዋ የህብረተሰብ ተወካዮች ተናገሩ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ትናንት በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በየደረጃው ከሚገኘው የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የተወከሉት ግለሰቦች በቡድን በቡድን ሆነው ውይይትን እያካሄዱ ነው።
ተሳታፊዎቹ የአጀንዳ ማሰባሰቡን ሂደት አስመልክተው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረው አገራዊ የምክክር ጉዞ ዜጎች ተመካክረው በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲፈጥሩና እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያስችላል።
የድሬዳዋ ከተማ የወረዳ አምስት ህብረተሰብ ተወካይ አቶ በለጠ ተፈራ እንደተናገሩት፤ ሂደቱ በመመካከር እና በመደማመጥ የሀገር ዘላቂ ሰላም እና ጥቅሞችን በማስጠበቅ የተሻለች አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል።
ከጦርነት የምናተርፈው ነገር የለም ያሉት አቶ በለጠ ከዚህ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን በመመካከር ለሀገር ጥቅሞች እና አንድነት መትጋት ይገባናል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ለሰነቃቸው ዓላማዎች መሳካት ኃላፊነታቸውን በትጋት እንደሚወጡ በመግለፅ።
በድሬዳዋ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ መሐመድ ሙሴ በበኩላቸው ችግሮቻችንን በውይይት በመፍታት ለሀገር ዘላቂ እና ብሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ሁላችንም መትጋት ይገባል ብለዋል።
የትናንትም ሆነ አሁናዊ ችግሮች መሻገር የሚቻለው በመመካከር እና በመደማመጥ ብቻ መሆኑን በማስታወስ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይዞ የተነሳቸው ዓላማዎች የምንፈልጋትን ጠንካራ አገር ለመገንባት ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ በህይወት ዘመኔ ያጠራቀምኩትን ሀገራዊ ሐሳቦች በሙሉ ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
በሰከነ መንገድ፣ በመደማመጥ እና በመከባበር ችግሮችን መፍታት እና ቀጣዩን የጋራ ጉዞ ማሳመር መንፈሳዊም ምድራዊም አጀንዳ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ሰብሳቢ ወንድም ሚልኪያስ ታዬ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመራቸው ተግባራት በመመካከር ያሉንን መልካም ስራዎችና ተስፋዎች ለማስቀጠል እንዲሁም ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ በመመካከር የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።
አካል ጉዳተኛዋ ሶፊያ ዱሪ በበኩሏ አገራዊው የምክክሩ ሂደት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ማካተቱ እና የሁሉም ዜጋ ድምፅ በእኩል እንዲሰማ ማድረጉ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ የሆነ ስምምነት ለመፍጠር ያስችላል ብላለች።
በተለይም አካል ጉዳተኞች በአገር ሁለንተናዊ ጉዞዎች ላይ እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እንዲረጋገጥ ሀገራዊው ምክክሩ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግራለች።
በአጀንዳ ማሰባሰቡ ውይይት ላይ የህዝቡን ፍላጎትና ቀጣይ ምኞት በሚገባ በማስጨበጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል ተሳታፊዎቹ።