የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ቀደመ ከፍታው እንዲመለስ ችግሮችን በመለየት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ቀደመ ከፍታው እንዲመለስ ችግሮችን በመለየት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ቀደመ ከፍታው እንዲመለስ ችግሮችን በመለየት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቤተ መንግስት የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሄዷል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ መድረክ በመወከልና በመሳተፍ የኢትዮጵያ ስም እንዲጠራ ያደረጋችሁ አትሌቶች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ከአትሌቶቹ ጀርባ በመሆን አስተዋጽኦ ያበረከቱ አሰልጣኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አትሌቶቹ በውድድሩ በነበራቸው ተሳትፎ የአቅማቸውን ጥረት በማድረግ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያዎችን በማምጣታቸው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በመሆኑም የሚሰጠው ሽልማትና እውቅና አትሌቶች የኢትዮጵያ እንቁዎች በመሆናቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ታምራት ቶላ እኔ ታምሚያለሁ አንተ ተወዳዳር በማለት የግል እድሉን ለኢትዮጵያ ውጤት ሲል የሰጠው አትሌት ሲሳይ ለማ ክብርና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በዓለም እንድትታወቅ ያስቻለና ስፖርቱ ከሕዝብ ጋር ጥብቅ የስሜት ቁርኝት ያለው መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ አንስተዋል።
በፓሪስ ኢሊምፒክ የተደረገውን ውድድር ኢትዮጵያዊያን በቅርበት መከታተላቸውን ገልጸው በውድድሩ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለመመዝገቡን አንስተዋል።
የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1 የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ መገኘቱ ያሉብንን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ያመላከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ያላት ውጤት ከዚህ በላይ እንዳይንሸራት ቀድሞ ወደነበረበት ከፍታ እንዲመለስ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በንግግር፣ በመከባበርና በመደማመጥ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበው
በስፖርቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ መንግስት የውጤት መቀዛቀዝን ጨምሮ በስፖርቱ መስክ ያሉ ችግሮች ጥናትና ውይይትን መሰረት አድርጎ እንዲፈታ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በስፖርቱ የአሰራር፣ አመራር፣ በአደረጃጀትና የሕግ ማዕቀፍ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ የተገኘው ውጤት ሕዝቡ በሚጠብቀው ልክ ባይሆንም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም በፓሪስ ኦሊምፒክ የተገኘው ውጤት በቀጣይ ብዙ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ያመላከተ መሆኑን አንስተዋል።
በውሃ ዋና ስፖርት የተወዳደረችው ሊና አለማየሁ፤ በኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በመወከል ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏ የላቀ ደስታ እንደተሰማት ገልፃለች።
በተወዳደረችበት 50 ሜትር ሴቶች ነጻ ቀዘፋ ብሔራዊ ክብረ ወሰን ማሻሻሏም ልዩ ስሜት እንደፈጠራባት ተናግራለች።
በ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር ስድስተኛ የወጣው ምስጋና ዋቁማ፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በማትታወቅበት ውድድር ባመጣው ውጤት መደሰቱን ተናግሯል።
በቀጣይም ከተሰራበት ከዚህ በላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያረጋገጥንበት ውድድር ነው ብሏል።
በእለቱ ጉዳት ላይ በመሆኑ የመወዳደር እድሉን ለታምራት ቶላ የሰጠው አትሌት ሲሳይ ለማ፤ ከግለሰብ ጥቅም ይልቅ የሀገርና የሕዝብ አደራ በማስቀደም የወሰነው መሆኑን ተናግሯል።
በዚህም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡኝ እውቅና እና ምስጋና ተደስቻለሁ ብሏል።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ መንግስት በኦሊምፒኩ ውጤት ላመጡና ለተሳተፉ አትሌቶችና አሰልጣኞች ሽልማት አበርክቷል።
በኦሊምፒኩ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች ማራቶን ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ የ7 ሚሊዮን ብርና የወርቅ ኒሻን ሽልማት አግኝቷል።
በሴቶች ማራቶን፣ በ800 ሜትር ሴቶችና በ10000 ሜትር ወንዶች የብር ሜዳሊያ ያገኙት ምክትል ኮማንደር አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ አትሌት ፅጌ ዱጉማና አትሌት በሪሁ አረጋዊ በተመሳሳይ የ4 ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝተዋል።
በልዩ ተሸላሚ ዘርፍ በወንዶች ማራቶን በ42 ዓመቱ የሮጠው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 50 ግራም የወርቅ ኒሻንና በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ በመጨረሻው ዙር በመሰናክል ተጠልፎ የወደቀው ዋና ኢንስፔክተር አትሌት ለሜቻ ግርማ የ2 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
ሌሎች አትሌቶችና አሰልጣኞች እንደ ተሳትፏቸው ደረጃ ከ50 ሺህ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል።
ኢትዮጵያ በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።