በክልሉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማነት መረባረብ ይገባል- ዶክተር አህመዲን መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማነት መረባረብ ይገባል- ዶክተር አህመዲን መሀመድ
ደሴ ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተቀናጀ አግባብ መረባረብ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድ ገለጹ።
የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
ዶክተር አህመዲን መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳመለከቱት፤ ክልሉ ያለውን ሀብት በመጠቀምና ጠንክሮ በመስራት ከተረጅነት ለመውጣት ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል።
በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አበረታች የስራ እድል መፈጠር መቻሉን ጠቁመው፤ በአዲሱ በጀት ዓመት ሁሉም በየአካባቢው ያለውን ፀጋ፣ ሀብትና አቅም በመጠቀም ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይ የአመራር አባላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ተቋማትንም በማዘመንና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ስቡህ ገበያው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ከሌሎች ተቋማት ጋር ጭምር በመቀናጀት ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤታማ ተግባር መከናወኑን አመልክተው፤በቀጣይም በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ ስልጠና በመስጠት በክህሎት የተደገፈ የስራ እድል ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ ከ980 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የገለጹት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ናቸው።
ከባለፈው ዓመት ልምድ በመውሰድ በአዲሱ በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።
እንደ ምክት ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያም ፤ ለአዲሱ የበጀት ዓመት ከሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ፣ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም ለማመቻቸት ከወዲሁ እየተሰራ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በበኩላቸው፤ በዞኑ የተሻለ የስራ እድል ለመፍጠር በቅንጅት ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ ከ143 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከዕቅድ በላይ እንደተከናወነ አስታውሰው፤ በአዲሱ በጀት ዓመትም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ላቂያው አንዳርጌ በበኩላቸው እንደገለጹት፤በተጠናቀቀው በጀት ከ51 ሺህ ለሚበልጡት ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ከዕቅድ በላይ መፈጸም ተችሏል።
በቀጣይ የራሳችንን አቅም ተጠቅመን የተሻለ የስራ እድል ለመፍጠር እንሰራለን ሲሉም አስታውቀዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።