የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ልኡካን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ልኡካን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ልኡካን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ነሐሴ 8 እና 9 ቀን 2016 ዓም በአዲስ አበባ ስለሚካሄደው የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም የመከሩ ሲሆን ፎረሙ የግብርና ኢንቨስትመንት እድሎች ጎልተው የሚታዩበት እንደሆነ ተመላክቷል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ፣ የመስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞች በተገኙት ምርጥ ተሞክሮዎች ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰማቸውን አብራርተዋል፡፡
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ረጅም እድሜ ያስቆጠረ አጋር የልማት ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው ግብርና ሚኒስቴር በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ባስመዘገባቸው ውጤቶች ውስጥም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ብሔራዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረሙ በተለዩት ዋና ዋና መስኮች በግብርና ሜካናዜሽን፣ በመስኖ ስንዴ ልማት፣ በአፈር ጤና፣ በእንስሳት መኖ ልማት እና በእንስሳት ልማት ላይ ባለሀብቶች በቂ ግንዛቤ አግኝተው እንዲሰሩ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና የኢኮኖሚ አማካሪ ማክሲሞ ቶሬሮ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኑንና በውጤቱም መደሰታቸውን ገልፀው ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡