በክልሉ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በክህሎትና በተግባር የዳበረ ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይል የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በክህሎትና በተግባር የዳበረ ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይል የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው
ደሴ፤ ነሐሴ 7/2016 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችን በማዘመንና በመደገፍ በክህሎትና በተግባር የዳበረ ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይል ከማፍራት ባለፈ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በዘላቂ የሥራ እድል፣ በኢንተርፕርነርሺፕና በኢንተርፕራይዝ ልማት ፕሮግራም ላይ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
የቢሮው ኃላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) እንደገለፁት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን በመደገፍና በማዘመን በክህሎትና በተግባር የዳበረ ሥራ ፈጣሪ ብቁ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው።
እንዲሁም ኮሌጆቹ በኢንተርፕርነርሺፕ በግብዓትና በሰው ኃይል በልጽገው ሃብት ማመንጨት ጭምር እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉን ፀጋ በመለየት የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ ተሻለ ዕድገት መሸጋገር ይኖርብናል ብለዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው፤ በፕሮግራሙ ተግባርና ክህሎት ተኮር ስልጠና በመስጠት ብቁና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ለዚህም በክልሉ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የአካባቢውን ፀጋና ሀብት ለይተው በልዩ ሁኔታ ማሰልጠን እንዲችሉና የንግድ ፍቃድ ጭምር አውጥተው ኢንተርፕርነር መሆን እንዲችሉ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ኮሌጆቹ በቴክኖሎጂ ዘምነው በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአውቶሞቲቭ፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎች ግብዓት አሟልተው ከማሰልጠን ባለፈ የራሳቸውን የውስጥ ገቢ እንዲያሳድጉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ በ15 ኮሌጆች በልዩ ሁኔታ ከ300 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በማደራጅት በተግባር ተኮር ስልጠናና ክህሎት በልጽገው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በፕሮግራሙ ኮሌጆችን በማሻሻል በተግባር ስልጠና ብቁና ተፎካካሪ ትውልድ ይገነባል።
ኮሌጆቹ ግብዓትና የሰው ኃይል አሟልተው ተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት ስራ ፈጣሪ ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉም ይደረጋል ብለዋል።
''ኮሌጁን በቴክኖሎጂ በማዘመን ክህሎትና ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት የበቃ ስራ ፈጣሪ ትውልድ የመገንባት ስራ በቅንጅት እየተከናወነ ነው'' ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን አቶ ኤርሚያስ ጌትነት ናቸው።
በመድረኩ አመራሮች፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።