ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በሆርቲካልቸር ንግድ መተሳሰር የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በሆርቲካልቸር ንግድ መተሳሰር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። 

ስምምነቱን በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ፣ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ነጋ መኳንንት እንዲሁም የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ሙኩካ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረባቸውና ያልተጨመረባቸው የሽንኩርት፣ አቮካዶና ድንች ምርቶችን ወደ ኮሜሳ አባል አገራት እንደምትልክ ተጠቁሟል። 

ስምምነቱ በኮሜሳ አባል አገራት መካከል ንግድን ለማጠናከርና ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደነዚህ አገራት ለመላክ ብሎም አባል ሀገራቱ ወደ ኢትዮጵያ ምርቶቻቸውን እንዲልኩ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ ስምምነቱ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ውስጥ የሆርቲካልቸር ንግድን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርትን በተደራጀ አሰራር ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ ለመላክም  እንደሚያግዛትም ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረባቸውና ያልተጨመረባቸው ሽንኩርት፣ አቮካዶና ድንች ምርቶችን ወደ ኮሜሳ አባል አገራት እንደምትልክ ገልጸዋል። 

የተደረገው ስምምነት አባል አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግና የኢትዮጵያን ባለሃብቶች ከአባል አገራት ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ በጋር እንዲሰሩ ያስችላልም ብለዋል፡፡

ለስምምነቱ ተግባራዊነት የዘርፉ ተዋናዮች በትጋት መስራት እንዳለባቸው ገልጸው ግብርና ሚኒስቴር ሁኔታዎችን በማመቻቸት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው ስምምነቱ የአምራቾችን አቅም ለመገንባት፣ ጥራት ላይ ለመስራት፣ የሚያጋጥሙ የሎጅስቲክ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው በቀጣናው የበለጠ ተፎካካሪ ለመሆን እንደሚሰሩ ጨምረዋል።

በኮሜሳ አባል አገራት መካከል የሆርቲካልቸር ንግድን በማፍጠን ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ጥምረት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ጆን ሙኩካ ናቸው።

በመርሀ ግብሩ ዓለም አቀፉ የልማት አጋር ድርጅቶች፣ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ጥምረት ተወካይና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም