የትኛውንም ግዳጅ በብቃት በመወጣት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የትኛውንም ግዳጅ በብቃት በመወጣት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት በመወጣት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በ12ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር የሠራዊት አባላትን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ የመከላከያ ጀኔራል መኮንኖች እና የሠራዊቱ አባላት ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በርካታ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና ውጣ ውረዶችን በብቃት በመወጣት ለምርቃት የበቁ የልዩ ኃይል አባላትን እንኳን ደስ አላቹህ ብለዋል።
በየፈርጁ የተደራጁ የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀቶች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና እና ህዝቦቿ የመጨረሻ ምሽግ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ልዩ ኃይል ለየት ያለ ሀገራዊ ኃላፊነትና አደራን በመሸከም በተሰጠው ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የላቀ ሥነ-ምግባርን የተላበሰ የኢትዮጵያ የሰላም ዘብ መሆኑን አብራርተዋል።
ለምርቃት የበቁ የልዩ ኃይል አባላትም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቀድመው በመገኘት ግዳጃቸውን በብቃት የሚወጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት በመወጣት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስተማማኝ ዘብ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፥ በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቁ የልዩ ኃይልና ጸረ-ሽብር አባላት ላለፉት ወራት የተሰጣቸው ወታደራዊ ሳይንስ በጠላት ፊት ለፊትና ጀርባ በመግባት የሚሰጣቸውን ግዳጅ መወጣት የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ፥ ተመራቂዎቹ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸውን አቅም በመፍጠር የዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ መደረጉን በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።
ለዚህም ምሩቃኑም የሀገርን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ቀጣይ የመሰጣቸውን ግዳጅ በላቀ አፈፃጸም መወጣት የሚያስችል ፈታኝ የተግባርና ንድፈ ሃሳብ ትምህርት መከታተላቸውን ገልጸዋል።
ለምርቃ የበቁት የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር የሠራዊት አባላትም "አዳኞቹ" የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን፤በቆይታቸው የትኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም ማጎልበታቸው ተገልጿል፡፡