ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክልል ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰሩ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን ከክልል ከተሞች በአየር ትራንስፖርት ከማስተሳሰር ባሻገር የክልል ከተሞች እርስ በርሳቸው እንዲገናኙ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ከማስፋት ባሻገር የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይም  ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ከተሞች መዳረሻዎችን ከማስፋት በተጨማሪ የክልል ከተሞችን እርስ በርሳቸው በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ሥራ የደንበኞችን ፍላጎትና ጥናትን መሰረት በማድረግ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡም አየር መንገዱ ባህር ዳርን ከደሴና ኮምቦልቻ፣ ጅግጅጋን ከጎዴ፣ መቀሌን ከሽረ እንዲሁም ጋምቤላን ከአሶሳ በአየር ትራንስፖርት እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰሩ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት። 

የደብረ ማርቆስ ኤርፖርት ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከባህር ዳር ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ማጠናከር ለንግድ፣ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ሥራ መጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።  

ይህንንም ከግምት በማስገባት የክልል ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት እርስ በርሳቸው የማስተሳሰር ሥራ በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት 139 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም