ቀጥታ፡

ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት በሚደረገው የህልውና ትግል የላቀ ሚናችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት በሚደረገው የህልውና ትግል የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም በመመከት እስከ 2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብ የመገንባት ግብ ይዛለች፡፡

የተረጅነት እሳቤን በማስወገድ ለአደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡

ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት በሚደረገው ጥረትም የመገናኛ ብዙኃን ሚናቸውን እንዲወጡ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማኒጂንግ ኤዲተር ወንደሰን ሽመልስ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሀዋሳ ቅርጫፍ ከፍተኛ አዘጋጅ እንዳለ ደበላ፤ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ አደጋዎችን በራሷ አቅም መቋቋም የሚያስችል ጸጋ እንዳላት ገልጸዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ሰፊና ለም መሬት፣ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ እንዲሁም ሁሉን አብቃይ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም ሃብቷን በአግባቡ አልምታ ሳትጠቀም መቆየቷን ጋዜጠኞቹ አንስተዋል።

አሁን ላይ ግን የሀገርን እምቅ አቅሞች የመጠቀምና በራስ አቅም የመረዳዳት ባህል እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ህብረተሰቡ ያሳየው ትብብር በራስ አቅም መቆም እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ሂሩት አለሙ፤ የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል ተቋማዊ ሆኖ እንዲዳበር በማድረግ ተረጅነትን ማስወገድ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በተበጣጠሰ መንገድ ያለውን አሰራር ቅርፅ በማስያዝ ለተጀመረው ትግል መሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከተረጅነት አሰተሳሰብ የማውጣት ትልሟን ታሳካ ዘንድ የመገናኛ ብዙኃን እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተረጅነት አስተሳሰብ ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ነፃነትን የሚጋፋ አሳፋሪ እሳቤ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄንን ህብረተሰቡ በልኩ እንዲረዳው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አደጋን በራስ አቅም መመከት እንደሚቻል ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ሀገራዊ አደራችንን ለመወጣት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል። 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ ማህበረሰቡ ችግሮች ሲከሰቱ ተረዳድቶ የማለፍ እሴት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ እነዚህን እምቅ ማህበረሰባዊ እሴቶች አጉልቶ በማውጣት ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት ብሔራዊ አጀንዳ በመሆኑ ለሁሉም በቂ መረጃና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም