ቀጥታ፡

የኮማንዶና የአየር ወለድ ዕዝ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ሀይሎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 7/2016 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የኮማንዶና የአየር ወለድ ዕዝ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ሀይሎችን አስመርቋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን  ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። 

በኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ስር የሚገኘው የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዳኞቹ በሚል መጠሪያ ያሰለጠናቸውን አሥራ ሁለተኛ ዙር የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ሀይሎችን  ነው ያስመረቀው።


 

ተመራቂዎቹ ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በግዳጅ አፈፃፀማቸውና በዲሲፕሊናቸው የተመረጡና የተሰጠውን አስቸጋሪ ስልጠና በአጥጋቢ ሁኔታ ያጠናቀቁ ናቸው።

ተመራቂዎቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በተናጠልም ሆነ በቡድን ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስልጠና የወሰዱ መሆናቸው ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ በተመራቂ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር አባላቱ የተለያዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች የቀረቡ ሲሆን በክብር እንግዳው የተመራው የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችም በዕዙ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ የአረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም