ቀጥታ፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶች ኢትዮጵያን ለማስጠራት ላደረጋችሁት ጥረት ምስጋና ይገባችኋል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶች ኢትዮጵያን ለማስጠራት ላደረጋችሁት ጥረት ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ተደርጎለታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ አትሌቶች ሁሌም በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ ባንዲራና ስም ከፍ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓሪስ ኦሊምፒክም ለሀገራችሁ ውጤት ለማምጣት የሚቻላችሁን ሁሉ ጥረት አድርጋችኋል፣ ምስጋናም ይገባችኋል ብለዋል።

ለአትሌቲክሱ ውጤታማነት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በወንዶች ማራቶን ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ታምራት ቶላ በውድድሩ የአየር ሁኔታው ፈታኝ ቢሆንም በቡድን ስራ ውጤቱ ሊገኝ እንደቻለ ገልጿል።


 

ለኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣቱ ትልቅ ደስታና ክብር እንደሚሰማው ተናግሯል።

በስፍራው የተገኘው ጀግናው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ስለሰጠው ብርታትና በጉዳት ምክንያት ሳይወዳደር ለእርሱ እድሉን ላመቻቸለት አትሌት ሲሳይ ለማ ምስጋናውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሸኛኘት አንስቶ እስከ አቀባባል ድረስ ላደረገው ድጋፍና ላሳየው አጋርነትም አመስግኗል።

በሴቶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ በውድድሩ ላይ ባስመዘግበችው ውጤት ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።

በትውልድ ኢትዮጵያ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን ባልገፈተር የወርቅ ሜዳሊያውን አገኝ ነበር ያለችው አትሌቷ ያገኘችውን ውጤት በፀጋ እንደምትቀበል ገልጻለች።


 

በ800 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ፅጌ ዱጉማ፤ ከምንም በላይ የሀገር አደራ በማስቀደም የሚቻላትን ጥረት በማድረግ ሜዳሊያ በማግኘቷ መደሰቷን ተናግራለች።

በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የብር ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት በሪሁ አረጋዊ፤ በውድድሩ አስቀድመን የተነጋገርንበትን የቡድን ስራ ለመተግበር ጥረት አድርገናል ብሏል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ለልዑካን ቡድኑ ላደረገው አቀባበልና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በብሔራዊ ቤተ መንግስት የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚደረግለት ከወጣው መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ልዑካን ቡድኑ ትናንት ፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሽኝት እንደተደረገለት ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ 1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎች በማግኘት 47 ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም