የኢትዮጵያ አትሌቶች በስፖርት ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት ትልቅ አሻራ እያኖሩ ነው - አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቶች በስፖርት ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት ትልቅ አሻራ እያኖሩ ነው - አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቶች በስፖርት ዲፕሎማሲ መስክ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ማህሌት ኃይሉ ገለጹ።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሽኝት ተደርጎለታል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ማህሌት ኃይሉ፣ በሀገሪቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የዲፕሎማሲው አንዱ ምሰሶ በሆነው የስፖርት ዲፕሎማሲ አትሌቶች የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት እያኖሩት ያለው አሻራ ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ መሆኑን አምባሳደር ማህሌት ገልጸዋል።
በፈረንሳይ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ከአቀባበል አንስቶ እስከ ሽኝቱ ለአትሌቶች ላደረጉት ድጋፍና ማበረታቻ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ኤምባሲውና ዳያስፖራው አትሌቶች በፓሪስ በነበራቸው ቆይታ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።
ኦሊምፒኩን ለመከታተል ከአውስትራሊያ ወደ ፈረንሳይ የመጡት አቶ በላይነህ ፋንታሁን የተሰኙ ግለሰብ በቤተሰባቸው ስም ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድኑ ያዘጋጁትን የዋንጫ ስጦታ አምባሳደር ማህሌት ለረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ለአትሌቶቹ ማበርከታቸውን ኢዜአ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የኦሊምፒክ ውድድር ትናንት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ 1 የወርቅና 3 የብር አጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በተያያዘም የልዑካን ቡድኑ ነገ ማለዳ አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል እንደሚደረግለት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጨማሪም ለልዑኩ ነገ ከሰዓት በብሔራዊ ቤተ መንግስት የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ይካሄዳል።