በከተማው የተጀመሩ ነባርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ለህዝቡ የልማት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው--አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የተጀመሩ ነባርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ለህዝቡ የልማት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው--አቶ መላኩ አለበል
ጎንደር ፤ ነሐሴ 6/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴራል መንግስት ለጎንደር ከተማ ልማትና እድገት መፋጠን ያስጀመራቸው ነባርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ለህዝቡ የረጅም ዓመታት የልማት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለፁ።
ሚኒስትሩ በከተማው የተጀመሩ ነባርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን የአፈጻጸም ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በከተማው የተጀመሩ ነባርና አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየው የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ስራን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመረከብ እያከናወነ ያለው የግንባታ ስራ አበረታች መሆኑን በማከል፡፡
የተጀመረው የኮሪደር ልማትም የከተማውን ልማት በማፋጠን የጎላ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፤ የልማት ስራው ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የዓጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ የጥገና ስራው መጀመሩ ቅርሱን ከመፍረስ አደጋ የሚታደግ ከመሆኑም በላይ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳለጥ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
የልማት ፕሮጀክቶቹ ለፍጻሜ እንዲበቁ ህዝቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎና ርብርብ የሚደነቅ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ የከተማው አመራርና የፕሮጀክቶቹ ተቋራጮችም ሃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ ናቸው ብለዋል።
ለልማት ፕሮጀክቶቹ መሳካት ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም እያደረገ ያለው የሰላም ጥረት ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ገልፀዋል፡፡
መንግስት የልማት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም የከተማውን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
የፕሮጀክቶቹ አሁናዊ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በጥራት እንዲጠናቀቁ የተጀመሩ ጥብቅ የክትትል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያነቃቁ ናቸው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው፡፡
በየደረጃው ያለው አመራር በየጊዜው የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እያገዘ ነው ብለዋል፡፡
የከተማው ነዋሪ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እያደረገ ያለው ትብብርና ተሳትፎ አበረታች መሆኑን እና ይህንኑ ተግባርም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሩና የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት በተሳተፉበት ጉብኝትም የአባይ የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ፋብሪካ የምርት እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል፡፡