በድሬዳዋ ለሀገራዊው ምክክር የሚጠቅሙ መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰብበት ምክክር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ለሀገራዊው ምክክር የሚጠቅሙ መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰብበት ምክክር እየተካሄደ ነው
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 6/2016 (ኢዜአ)፡- በሀገራዊው ምክክር ላይ ያጋራ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸው መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበት የምክክር ሂደት በድሬዳዋ አስተዳደር እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይቱን በመሳተፍ ላይ ያሉት ከአስተዳደሩ አራት የገጠር ክላስተሮች እና ዘጠኝ የከተማ አስተዳደሩ ወረዳዎች የተወጣጡና አስቀድመው ለአጀንዳ ማሰባሰቡ በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክሩ አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለሀገራዊው ምክክር የሚሆኑ መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰብበት ወሳኝ የምክክር ምዕራፍ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።
አጀንዳው የሚሰበሰበው እስከ 52 አባላት ባሏቸው 10 ቡድኖች መሆኑን ጠቅሰው፤ የየቡድኑ አባላት ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አካታች በሆነ መንገድ አወያይ እና ፀሐፊ መርጠው መሠረታዊ የሚሏቸውን አጀንዳዎች እያሰባሰቡ ናቸው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ ከአራት ገጠር ክላስተሮች እና ከዘጠኝ የከተማ አስተዳደሩ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ወኪሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን በማስታወስ።
በሂደቱ በአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መምህራን ፣ ዕድሮች፣ ነጋዴዎች እና በሌሎች አደረጃጀቶች የተወከሉት የህብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማደራጀት ስራቸውን እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2016ዓ.ም ድረስ እንደሚያጠናቅቁ ተመልክቷል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ዛሬ በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።