ቀጥታ፡

መንግስት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጀመራቸው ምክክሮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን የሚያጠናክሩ ናቸው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/ 2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው የምክክር መድረኮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን የሚያበረታታ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በቅርቡ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ምክክር ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከዚህ ቀደም  የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ብዙ ችግሮች ያሉበትና የመወያየት ባህል ያልዳበረበት ነበር ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ሀገር ለበርካታ ችግሮች ተዳርጋ መቆየቷን ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በልሂቃን መካከል በሰጥቶ መቀበል መርህ ተቀራርቦ የመስራት ባህልና ልምምድን ማዳበር እንደሚገባ ግንዛቤ እየተፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።  

ምክር ቤቱ ችግሮችንና የፖለቲካ ልዩነትን በውይይት በመፍታት መተማመን ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

መንግስት የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት የጀመራቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ለአብነትም የፌደራልና የክልል መንግስታት በሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ፣ የልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ገንቢ ምክክር ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ምክክርም በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን በማጠናከር ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስለሚኖር ትብብር፣ በፖለቲካ ምኅዳር፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን አመላክተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከመንግስት ጋር በየደረጃው የሚያደርጉት ምክክርም ግልጽነትን በመፍጠር ለሚያጋጥሙ ሀገራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም