በአዴት ከተማ የክፍለ ጦሩን ወታደራዊ ቤዝ ለማጥቃት የመጣው ፅንፈኛ ተደመሰሰ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2016(ኢዜአ)፦በሰሜን ጎጃም ዞን አዴት ከተማ የምስራቅ ዕዝ ክፍለ ጦርን ወታደራዊ ቤዝ ለማጥቃት የመጣው ፅንፈኛ መደምሰሱን ክፍለ ጦሩ ገለጸ።

በዞኑ የተሰማራውን የምስራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር ከአራት አቅጣጫ ሀይሉን አሰባስቦ አዴትን ለመቆጣጠርና ወታደራዊ ቤዙን ለማጥቃት በእብሪት ተገፋፍቶ የመጣውና አመራሮቹን ጨምሮ 57 የፅንፈኛው ቡድን አባላት ሲደመሰስ 23 ማቁሰሉን ክፍለ ጦሩ አስታውቋል።

የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮሎኔል አለም ታደለ ፅንፈኛው በሰሜን ጎጃም በሰራዊቱ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሠበት በመሆኑ ቁርስ አዴት ምሳ ባህር ዳር በሚል እብሪት በአራት አቅጣጫ አዴትን ለመቆጣጠር የመጣው ሀይል መደምሰሱን ነው የተናገሩት።

ኮሎኔል አለም ከዚህ ቀደም በክፍለ ጦሩ እርምጃ በተወሰደበት አንሙት በተባለ ቀንደኛው የፅንፈኛ አመራር ስም ዘመቻ ለመክፈት ከመራዊ፣ ከሰከላ፣ ከገርጨጭ፣ በሮብ ገበያ አድርጎ አዴት የተንቀሳቀሰ ሃይል መደምሰሱን ገልጸዋል።


በተመሳሳይም ከመራዊ፣ ብራቃት፣ ዴንሳ ባታ በማድረግ መዳረሻውን አዴት ያደረገ፣ ከአርብ ገበያ፣ በዳባት ወደ አዴት ያቀናውና ከጭስ አባይ በችግኝ ጣቢያ፣ በፈረስ ወጋ በኩል ደብረ ማይ ላይ የበቀል ጥቃት ለመፈፀም የመጣው ሀይል በክፍለ ጦሩ ሰራዊትና በጥምር ጦሩ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል ነው ያሉት።

የቀጣናውን ጥምር ጦር በኮሚቴ የመሩት መዝገበ ሁንልኝ፣ ኢንስፔክተር መንገሻ አብዬና ረዳት ኢንስፔክተር እያዩ አለነ እንደተናገሩት በዘመቻ አንሙት ስም ቁርስ አዴት ምሳ ባህርዳር ለመብላት አልሞ የተንቀሳቀሰው እብሪተኛው የፅንፈኛ ሀይል አዴት ሳይደርስ በጥምር ጦሩና በክፍለ ጦሩ ነበልባሎች ከአፈር ተቀላቅሏል ሲሉ ገልፀዋል።

የጥምር ጦሩ ኮሚቴዎች የፅንፈኛው ሀይል አዋጊዎች ቻሌ መንግስቴ ልዩ ሀይል የነበረ ሻለቃ አመራር፣ ሙሉአለም ልዩ ሀይል የነበረ ሻለቃ ምክትል፣ ቻይና አዳምጤ ሻምበል አመራር እርምጃ ሲወሰድባቸው 7 የጦር መሳሪያ፣ የወገብና የደረት ትጥቆች፣ በርካታ ቦምቦችና ጥይቶች ተማርከዋል ብለዋል።


 

እንዲሁም በጎንጂ ቆለላ ሸበሌ ቀበሌ ከመሸንቲ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ልዩ ስሙ ኤሎማ በተባለ ቦታ ካምፕ መስርቶ ባህርዳርን ሲረብሽ የነበረው ፅንፈኛ በክፍለ ጦሩ አንድ ሬጅመንት ጥቃት በመፈፀም አራቱ እርምጃ ሲወሰድባቸው ከህብረተሰቡ የዘረፋቸው 24 ሞተር ሳይክሎችን በመማረክ ካምፑንም ማቃጠል ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም