ቀጥታ፡

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲው ተረጅነትን ለማስወገድ ለሁሉም ክልሎች ኃላፊነትን ይሰጣል፤ ተጠያቂም ያደርጋል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 6/2016(ኢዜአ)፡- የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ተረጅነትን ለማስወገድ ለሁሉም ክልሎች ኃላፊነትን በመስጠት ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃን እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና ተጠናቋል፡፡


 

የተረጅነት አስተሳሰብን በማስወገድ ለአደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ጸድቋል፡፡

የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም በመሻገር እስከ 2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብ የመገንባት ግብ ተይዟል፡፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ የተረጅነት አስተሳሰብ ሀገራዊ ነፃነታችንን እየተፈታተነ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተረጅነት አስተሳሰብ ገዥ ሆኖ እንዲቀጥል የሚደግፉ ውስጣዊና ውጫዊ ኃይሎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለአደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጸጋና ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲው እና የማስፈፀሚያ ህጎች ሁሉም ክልሎች እነዚህን ጸጋዎች ተጠቅመው ከረተጅነት መላቀቅ የሚችሉበትን አሰራር የያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲው ሁሉም ክልሎች ያላቸውን ጸጋና ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተረጅነት አስተሳሰብን በማስቀረት፣ በሰላም ግንባታና አይበገሬነትን በግልና በጋራ መገንባት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስገድድና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ፖሊሲ ኃላፊነት ከመስጠት ውጭ በቂ የማስፈፀሚያ ህጎችና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ ስለሚወሰደው ርምጃ ያስቀመጠው ነገር አልነበረም ብለዋል፡፡


 

የተሻሻለው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ላሉ አካላት ኃላፊነት የሚሰጥ በአግባቡ ካለተወጡ ደግሞ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ግልጽ አሰራር የተካተተበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም