ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የተጀመሩ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች- ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የተጀመሩ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች- ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 6/2016(ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ዕድገት ኢኒስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው ።
ውይይቱ የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ረገድ ያለው ሚና እና የተገኙ ውጤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፥ በኢትየጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማከናወኗን ጠቅሰው፥ ዘንድሮም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
መርሐ ግብሩ ካስገኛቸው ውጤቶች መካከልም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ዘንድሮ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
አረንጓዴ አሻራ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ አሻራ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው የውሃ አካላት መጎልበት ዘርፈ ብዙ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
በተያዘው ክረምት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል ህዝብን ያሳተፈ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ በኩልም ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ያላትን ልምድ ለጎረቤት አገራት በማካፈል ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
የዓለም አቀፉ አረንጓዴ ዕድገት ኢኒስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ኦኬቹኩ ዳንኤል ኦግቦናያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ላይ እያከናወነች ያለው ተግባር ምሳሌ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም የግብርና ስርዓትን ለመገንባት በኢትዮጵያ የጀመራቸው ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢኒስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በአረንጓዴ ልማት የጀመረውን የትብብር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።