ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በድሬዳዋ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዛሬ በይፋ ጀመረ

ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 6/2016 (ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በድሬዳዋ አስተዳደር ለሀገራዊው ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዛሬ በይፋ ጀመረ።

በአጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ 13 ወረዳዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት፤ኮሚሽኑ ሀገራዊውን የምክክር ሂደት በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።


 

በአሁኑ ወቅት የሀገራዊው ምክክር ሂደቱ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን እና ለሀገር ዘላቂ ጥቅም እና አንድነት የሚበጁ የአጀንዳ ማሰባሰብ  በማካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

ዛሬም ከድሬዳዋ አስተዳደር የህዝብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋሉ የሚሏቸውን መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበት ምክክር በይፋ መጀመሩን አውስተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የመረጣቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወክለው የተገኙ ወኪሎች እና ባለድርሻ አካላት በነፃነት፣ በእኩልነት እና በመደማመጥ ለአገራዊው ምክክር የሚጠቅሙ መሠረታዊ አጀንዳዎች የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በመመካከርና በመወያየት የማይፈታ አንዳች ጉዳይ እንደሌለ ያስታወሱት  ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ፤ በዚህ በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረንና ተወያይተን ኢትዮጵያን አፅንተን እናቆማለን ብለዋል።

በመሆኑም  በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ላይ የሚሳተፉ አካላት  በትኩረት በነፃነት እና በመደማመጥ ታላቁን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማለት አስገንዝበዋል።

ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚካሄድ መሆኑም ተመላክቷል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ ከአስተዳደሩ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተመካክረው የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ያዘጋጃሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም