በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓሪስ ሽኝት ይደረግለታል - ኢዜአ አማርኛ
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓሪስ ሽኝት ይደረግለታል
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 6/2016 (ኢዜአ)፡- በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሽኝት ይደረግለታል።
ልዑኩ ነገ አዲስ አበባ ይገባል።
ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የኦሊምፒክ ውድድር ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና ስፖርት 38 ስፖርተኞችን አሳትፋለች። 1 የወርቅና 3 የብር አጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በአትሌቲክስ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በኦሊምፒኩ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ በፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ልዩ ሽኝት እንደሚደረግለት ኢዜአ ከኤምባሲው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፣ በሀገሪቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ይጠበቃል።
በፓሪስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና በፈረንሳይ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለልዑኩ አቀባባል ከማድረግ አንስቶ በውድድር ስፍራ በመገኘት አትሌቶችን በማበረታታት ድጋፍ አድርገዋል።
በተያያዘም የልዑካን ቡድኑ ነገ ማለዳ አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል እንደሚደረግለት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጨማሪም ለልዑኩ ነገ ከሰዓት በብሔራዊ ቤተ መንግስት የእውቅና መርሐ ግብር እንደሚካሄድም ተገልጿል።