በስደት ሀገር ያልተገኘን ስኬት በሌማት ትሩፋት! - ኢዜአ አማርኛ
በስደት ሀገር ያልተገኘን ስኬት በሌማት ትሩፋት!

(በቀደሰ ተክሌ - ሚዛን አማን ቅርንጫፍ)
የኑሮ ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ የማደግ ህልም አንግባ ነው የተነሳችው። ህልሟን እውን ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ስታማትር ቆይታለች። የኋላ ኋላ ግን ለሥራ ወደአረብ ሀገር መሄድን ምርጫዋ አደረጋልች።
ወይዘሮ ሞሚና ጀማል ትባላለች። ወደአረብ አገር የመሄድ የመጀመሪያ ምርጫዋ የተሳካ ቢሆንም ነገሮች አልጋ በአልጋ ስላልሆኑ ህልሟን እውን ለማድረግ ግን አልቻለም። ያ መንገድ ብዙ ድካምና ዋጋን ከማስከፈል ያለፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለመችው ስኬት ላይ ለመደረስ እንደማያስችላት ስትረዳ በሀገር ቤት ያለውን ጸጋ በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ተነሳሳች።
ለመለወጥ ሀገር ትቶ መሰደድ ያለውን አስቸጋሪ ውጣ ውረድ ዛሬ ላይ ለሌሎች ከሚናገሩ ሰዎች መካከል አንዷ ናት። በአረብ አገር የሰባት ዓመታት ልፋት ያላስመዘገበችውን ውጤት በሀገር ውስጥ የአካባቢዋን ጸጋ ለይታ በመንቀሳቀሷ በስኬት ጎዳና ብቅ ብላለች ወይዘሮ ሞሚና።
ወይዘሮ ሞሚና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የኩጃ ቀበሌ ነዋሪ ነች። ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ዛሬ ላይ አብዝታ የምትሻውን የቤተሰቦቿን ለም የእርሻ መሬት እንዲሸጥ አድርጋለች።
ሞሚና ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደአገር ቤት የተመለሰችው ሕይወቷን ለመቀየር የሚያስችል ወኔና እሳቤ ይዛ ነው። ከአረብ ሀገር ስትመለስ የከተማ ኑሮን አልመረጠችም። ይልቁንም ብዙ ወጣቶች ደፈርው የማይገቡበትን የገጠሩን ህይወት ተቀላቅላ ደፋ ቀና ማለትን ጀመረች። እንደ ሌሎች የመዋቢያ መሸጫ ሱቅ፣ ምግብ ቤት አሊያም የአልባሳትና ጫማ ቤት ከፍቶ መቀመጥን ልቧ አልፈቀደም። ለስደት ጉዞ ተሽጦ ከተረፈው የአባቷ ለም መሬት ላይ ዐይኗ ተተክሎ ቀረ እንጂ።
ወይዘሮ ሞሚና ከውጭ ሀገር ጉዞ መልስ ያሰበችው በሀገር ሀብት ሰርቶ መለወጥን ነው። በአካባቢዋም በቀላል ጉልበትና ገንዘብ ሰርቶ ለመለወጥ የሚያስችል ብዙ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለ ተገንዝባለች። ለእርሻ ሥራ፣ ለእንስሳት እርባታ እና ለንብ ማነብ ሥራ የሚሆን መሬት ይዘን እንደሌለን ሰው ተቸግሮ መታየት ልክ እንዳልሆነ ዛሬ ላይ ሆና ትናገራለች። ንግግሮቿም ቁጭት አዘል ናቸው። ቁጭቷን በሥራና በስኬት ለመወጣት ወስናለች። በግብርና ሥራ ከራሷ አልፎ የአካባቢውን ችግር ለመፍታት ቆርጣ ተነሳች።
በምትኖርበት አካባቢ የወተት እጥረት፣ የሥጋ እንስሳት ውድነት፣ የማር እና ሌሎች የግብርና ምርቶች እጥረት እንዳሉ አረጋገጠች። በቀዳሚነት ሰፊ ቤት ከሰራች በኋላ የወተት ላሞች እርባታ ሥራ ጀመረች። በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያሏት የወተት ላሞች ቁጥር 14 ያደረሰች ሲሆን፤ ከእነዚህ ላሞች መካከል በቀን ከ40 ሊትር በላይ ወተት የሚሰጧት ላሞች አሉ።
እንደ ላሞቹ ሁኔታ በትንሹ ስምንት ሊትር ከፍ ሲል 46 ሊትር የሚታለቡ አሏት። ወተታቸውም ከኩጃ አልፎ ለቢፍቱ እና ሚዛን አማን ከተሞች እየደረሰ ነው። ውሃና መኖ በጥሩ ሁኔታ ካገኙ የተሻለ ወተት ይሰጣሉ ትላለች። ወይዘሮ ሞሚና ይህንን የተረዳችው ደግሞ በስደት ከኖረችበት የአረብ ሀገር ተሞክሮ ነው።
"እጣ ፋንታሽ ነው የተባልኩ ይመስል እዚያም ሥራዬ ሆኖ ሰባት ዓመታትን ያሳለፍኩት በከብት እንክብካቤ ሥራ ነው" ትላለች። ያኔ በአረብ አገር እርሷ ለፍታ ቀጣሪዎቿ በሚያገኙት ውጤት ብትቀናም አሁን ላይ በራሷ ሰርታ በማሳካቷ ደስተኛ ነች።
በስደት ሀገር ሰርታ ባመጣችው ገንዘብ ላይ ጨምራ በሦስት ሚሊዮን ብር ሥራዋን ብትጀምርም የሌማት ትሩፋት ሥራዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታሏን ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ከፍ አድርጎታል። የተጀመረው የስኬት ጉዞ ይበልጥ ጠንክራ እንድትሰራ እያገዛት መሆኑንም ነው የገለጸችው። ከላም እርባታ በተጨማሪ ከ100 በላይ በግና ፍየል ገዝታ ማርባት ጀምራለች። ከ100 የማር ቀፎዎች ውስጥ በ30ው ላይ ንብ በማስገባት ወደምርት ለመሸጋገር እየተዘጋጀች ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የእንስሳት ማድለብ ሥራ ለመጀመር የሚያስችላትን ዝግጅትም እያደረገች መሆኑን ነው የገለጸችው።
ዋናው ነገር አመለካከትን ማስተካከል እንጂ ሴትነት ከማንኛውም ሥራ እንደማይገድብ በራሷ አረጋግጣለች። በወተት ልማት የመሰማራት ፍላጎት ኑሯቸው አቅም ያጡ የአካባቢውን ሴቶች የመደገፍ እቅድ አላት። ከአስቸጋሪው የአረብ ሀገር የስደት ኑሮ ተላቃ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር ተሰማርታ ውጤት እያገኘች በመምጣቷ ደስተኛ ነች።
“ባለን ሀብት ላይ ጉልበትና ጊዜያችንን አፍሰን ጠንክረን ከሰራን ለሌላው እንተርፋለን” የሚል ጽኑ እምነትም አላት።
ሰርቶ ለመለወጥ ወደወጭ ሀገር ስደትን ከመምራጥ በአገራችን ሰርተን መለወጥ እንችላለን የምትለው ወይዘሮ ሞሚና። ይህንንም ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ራሷ ሰርታ በመለወጥ በተግባር አረጋግጣለች። በአረብ አገር ሰርታ ያገኘቻትን መነሻ ጥሪት በአባቷ ጓሮ ለሌማት ትሩፋት በማዋልና ጠንክራ በመንቀሳቀሷ ዛሬ ላይ ካፒታሏን ማሳደግ ችላለች። ለሌሎች ወጣቶች ሥራ ከመፍጠር ባለፈ በምርቶቿንም ለአካባቢው ማኅበረሰብ እያደረሰች ነው።
“ነገን መልካም የምናደርገው በራሳችን ሀገር ሰርተን እንጂ ለሰው ሀገር በማገልገል አይደለም” በማለትም ትመክራለች። ይህንንም በአባቷ ጓሮ በሰራችው ውጤታማ ሥራ ያረጋገጠች ሲሆን፤ በቀጣይ ሥራዋን ይበልጥ ለማስፋፋት እየተዘጋጀች መሆኗን ትናገራለች። የእንስሳት መኖ ልማትም ቀዳሚ ዕቅዷ መሆኑን ነው የገለጸችው።
በወይዘሮ ሞሚና ዘርፈ ብዙ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ 29 ወጣቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ወጣት አሸናፊ ገዛኸኝ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች አንደኛው ነው። በወይዘሮ ሞሚና የላም እርባታ ውስጥ ላሞችን የመንከባከብ ሥራ ይሠራል። ከሚከፈለው ደመወዝ በተጨማሪ ጥቅማ ጥቅምም ያገኛል።
“ወይዘሮ ሞሚና ለሥራ ያላቸው ትጋት ለእኛ ትልቅ የሞራል እና የሥነ ልቦና ስንቅ ነው” በማለት ነው የሥራ ታታሪነቷን የገለጸው።
በተፈጠረለት የሥራ ዕድል በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን እያስተዳደረ መሆኑን የገለጸው ሌላው ወጣት ሐሰን በለጠ ነው። ከዚህ ቀደም የእለት ሥራ ሲያገኝ ብቻ እንደሚሠራ ያስታውሳል። አሁን ግን ወደዚህ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በቋሚነት የተሻለ ገቢ እያገኘ ነው።
"ወይዘሮ ሞሚና እንደ አሠሪ ሳይሆን እንደ እህት እያበረታታችን ከእኛ ጋር እኩል ስለምትሰራ ሥራውን ወደን በፍቅር እየሠራን ነው" ሲልም ተናግሯል።
ከወተት ምርቱ ተጠቃሚ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ንጉሤ ትዕዛዙ ከዚህ ቀደም ለሕጻናት እንኳ ወተት ማግኘት ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬ ግን ሕጻናት ብቻ ሳይሆኑ አዋቂዎችም በየቀኑ የሚፈልጉትን ያህል ወተት ማግኘት እንደሚችሉ ነው የገለጹት። በወይዘሮ ሞሚና ሥራ እርሳቸውም ተበረታተው በቀጣይ በጓሯቸው የሌማት ትሩፋት ሥራ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን አቅደዋል።
የወይዘሮ ሞሚና የሥራ እንቅስቃሴ በወተት ልማት ብቻ የቆመ አይደለም። በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ በመሰማራት ሁሉንም የሌማት ትሩፋት ውጤቶች ከአንድ ጓሮ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን በተግባር እንዳዩና ተሞክሮ እንደወሰዱም ነው የገለጹት።
የጉራፈርዳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ጨምደስ ወይዘሮ ሞሚና በሌማት ትሩፋት እያከናወኑት ያለው ተግባር ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆን ነው የሚገልጹት። ጽህፈት ቤቱ እርሳቸውን ለመደገፍ በተለያየ መንገድ ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ የእንስሳቱን ጤንነት የሚከታተል ባለሙያ መድቦ እየሰራ ነው።
እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፤ ወይዘሮ ሞሚና በሌማት ትሩፋት ዘርፍ መንግስት ያስቀመጠውን የልማት አቅጣጫ ከማሳካት ጀምሮ ለወጣቶች የፈጠሩት የሥራ ዕድል ቀላል የሚባል አይደለም። ቀጣይ ሥራቸውን በተሻለ ሁኔታ አስፋፍተው እንዲቀጥሉ አምስት ሄክታር መሬት ለመስጠትም በጽህፈት ቤቱ በኩል ዝግጅት መደረጉንም ነው የጠቆሙት።
ሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች ወደልማት ተቀይሮ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተፈጥሮ ጸጋ እና ይህን ጸጋ ማልማት የሚችል በቂ የሰው ኃይል አላት። ነገር ግን “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” እንደሚባለው ዛሬም በሀገሩ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ ወደ ምዕራቡ ዓለም እና የአረብ ሀገራት ዓይኑን የሚያማትር ወጣት ብዙ ነው።
ይህ አይነቱ እሳቤ እንደ ሀገር የሚያስከፍለውን ዋጋ መንግስት በመረዳት ዜጎች በሀገር ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን ሁኔታ እያመቻቸ ነው። ለወጣቶች ከገንዘብ ብድር ባለፈ መስሪያ ቦታ በማዘጋጀትና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ጭምር ለውጤት እንዲበቁ እየሰራ ይገኛል። በእዚህም በርካታ ሰዎች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ተግተው በመስራታቸው ኑሯቸውን ማሻሻልና መቀየር ችለዋል።
እንደ ወይዘሮ ሞሚና ያሉትም ለእዚህ አንድ ማሳያ ናቸውና በተለይ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደ ውጭ መሰደድን ሳይሆን የአካባቢን ጸጋ ማየትና መፈተሽን ልናስቀድም ይገባል። ለውጤታማነት ተግተን ከሰራን ደግሞ ስኬት በእጃችን ላይ እንደሆነ በራሳችን ማረጋገጥ እንችላለን።