ቀጥታ፡

የኦሊምፒክ የመዝጊያ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2016 (ኢዜአ)፦ የ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመዝጊያ ስነ ስርዓት በስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

የኦሊምፒኩ የመክፈቻ መርሐ ግብር በውድድሩ የ128 ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ መደረጉ ይታወቃል።

የሀገራት ልዑካን ቡድን አባላት በመርከብ ላይ በመሆን በሴን ወንዝ በማቋረጥ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ተካሄዷል።

የመዝጊያ ዝግጅቱ በስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም የሚከናወን ሲሆን አትሌቶች በመሮጫ መሙ ላይ በማለፍ ስንብት እያደረጉ ይገኛሉ።

በዘንድሮው ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች ማራቶን ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶሎና በሴቶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ በመዝጊያው ስነ ስርዓት የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለቡ በተመልካቾችና እንግዶች ፊት አልፈዋል።

በመክፈቻው በ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር ስድስተኛ በመውጣት አበረታች ውጤት ያመጣው አትሌት ምስጋና ዋቁማና በሴቶች የ50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ ውድድር የኢትዮጵያ ክብረ ወሰን የጨበጠችው ዋናተኛዋ ሊና አለማየሁ የኢትዮጵያን ባንዲራ መያዛቸው አይዘነጋም።

በመርሐ ግብሩ የኦሊምፒክ ባንዲራ 34ኛውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2028 ለሚካሄድበት ሎስ አንጀለስ የውድድር አዘጋጆች የማስረከብ ስነ ስርዓት ይከናወናል።

34ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2028 በሎስ አንጀለስ ይካሄዳል።

ከቀትር በፊት በሴቶች ማራቶን ፍጻሜ ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አትሌቶች ሜዳሊያ ይበረከታል።

አትሌት ትዕግስት ዛሬ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

ከ100 በላይ ዳንሰኞች፣ ትርዒት አቅራቢዎችና ሰርከሰኞች ስራቸውን ያቀርባሉ።

አሜሪካዊው ታዋቂ ራፐር ስኖፕ ዶግና አሜሪካዊቷ ድምጻዊ ቢሊ ኤሊሽን ጨምሮ የዓለማችን ታዋቂ ሙዚቀኞች በስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየም የሚያቀርቡት ስራ ለመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ድምቀት ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የፈረንሳዮቹ ፊኒክስና ኤር የተሰኙ ባንዶችም ስራቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፈረንሳይ ታሪክና ባህል የሚያሳዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና 38 ስፖርተኞች አሳትፋለች። 1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አሜሪካ በኦሊምፒኩ አንደኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። ቻይና፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያና አዘጋጇ ፈረንሳይ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ኬንያ በ4 የወርቅ፣ 2 የብርና 5 የነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከዓለም 17ኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

የሜዳሊያ ሰንጠረዡ በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር ተወዳድረው ሜዳሊያ ያገኙ ገለልተኛ አትሌቶችን አያካትትም።

ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በፓሪስ ሲካሄድ የቆየው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም