ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት የብሔራዊ ደህንነት፣ የማህበራዊ ፍትሕና የዘላቂ ልማት አጀንዳዎችን የማሳካት ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣት የብሔራዊ ደህንነት፣ የማህበራዊ ፍትሕና የዘላቂ ልማት አጀንዳዎችን የማሳካት ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን ከተረጅነት አስተሳሰብ መውጣትን የብሔራዊ ደህንነት፣ የማህበራዊ ፍትሕና የዘላቂ ልማት አጀንዳዎች መሆናቸውን ታሳቢ አድርገው መሥራት እንዳለባቸው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃን እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ የተረጅነት አስተሳሰብ የዜጎችን ነፃነትና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚሸረሽር መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀ የተረጅነት አስተሳሰብና ሥነ ልቦና በብዙዎች ዘንድ በራስ አቅም የመለወጥ ተስፋ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሃይል ተጠቅማ ከተረጅነት የምትላቀቅበት "የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ባሳለፍነው የካቲት ወር ተሻሽሎ እንዲጸድቅ መደረጉን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ እስከ 2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት ፖሊሲው የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለም አፈር፣ ሁሉን አብቃይ የሆነ መልክዓ ምድርና የአየር ጸባይ እንዲሁም አምራች የሰው ሃይል ያላት በመሆኑ ከተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ሰርቶ መለወጥ የሚገባ መሆኑን አንስተዋል።
የተረጅነት አስተሳሰብ የብሔራዊ ደህንነትና የሀገር ሉዓላዊነት ሥጋት በመሆኑ ሰርቶ ማደግና ችግርን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመው ፖሊሲው ብሔራዊ ደህንነት፣ ማህበራዊ ፍትህና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ አጀንዳ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመረዳዳት ባህልን በሥርዓት በማስተዳደር ዜጎች በራሳቸው ጸጋ ለአደጋ ምላሽ እንዲሰጡ የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሽን ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተረጅነት አስተሳሰብ ላይ የጋራ መረዳት ከተፈጠረ ለመጠባበቂያ እና እለት ደራሽ ክምችት የሚያስፈለገውን 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ሰብዓዊ እርዳታ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል ሀገራዊ አቅም እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚናው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ክብረ ነክ ከሆነ የተረጅነት እሳቤ የመውጫ መንገድ መሆኑን መረዳትም ይገባል ብለዋል፡፡
ከተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚችለበት አቅም መኖሩን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችም፤ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲውን ገቢራዊ በማድረግ ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፤ በኢትዮጵያ ሴፍትኔት ልምድ ተረጅነት ባህል ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩ ዘመናትን የተሻገረና ስር የሰደደ በመሆኑ ተከታታይ የአስተሳሰብና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቤል አዳሙ፤ የተረጅነት እሳቤ በብዙዎች ዘንድ የጠባቂነት አስተሳሰብ አሳድሯል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብዱራህማን ሩቤ፤ ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመውጣት አደጋ ከመድረሱ በፊት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ አጀንዳ በመቅረፅ የማህበረሰቡን አረዳድ በመቀየር ዜጎችን ከተረጅነት አስተሳሰብ ለማላቀቅ ሚናቸውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።