" አሎ " - ሰው የተከፈለበት ሰው የማዳን ጥሪ ! - ኢዜአ አማርኛ
" አሎ " - ሰው የተከፈለበት ሰው የማዳን ጥሪ !

በሀብታሙ መኮንን- ሀዋሳ ኢዜአ
ከአሰቃቂው እልቂት በስተጀርባ ነፍስን እስከ መስጠት የሚያደርሰውን የጎፋዎችን የአለኝታነት ጥግ ፍንትው አድርጎ ያሳየ የድረሱልኝ ጥሪ - " አሎ " ።
በጎፋዎች ዘንድ " አሎ " ከተባለ " አለሁ " ማለት ግድ ነው። ጥልቅ ደግነት፣ ሰው አክባሪነት፣ የልብ ወዳጅነትና የሀገርና ወገን አለኝታነት የጎፋ ህዝብ ሥነ-ልብና ከተገነባባቸው ምሰሶና ማገሮች መካከል በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው ።
ጎፋዎች ወገን በተቸገረ ፤ የከፋ ነገር በገጠመው ወቅትም "አለሁ" ብለው መድረስን ያውቁበታል ።
" አሎ " በጎፋዎች የይድረሱልኝ ጥሪ ነው ።
ይህንን ጥሪ የሰማ ሰው ምናልባት የከፉ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ ውስጥ ያለ፣ በሞት አፋፍ ያለ አልያም በሌሎች ምክንያቶች ሊደረስለት የሚገባ "ሰው" መኖሩን ያስተውላል። እናም ጨርቄን ማቄን ሳይል፣ ልጅ አዋቂ ፤ ብርቱና ደካማ ሳይለይ " አሎ " ወደተባለበት አቅጣጫ ይተማል ። ፈጥኖም ወገኑን ከአደጋ፣ ከሞትና ጉዳት ይታደጋል ። በዚህ ለሰዎች የመድረስ የሰውነት የማሳያ ጥግ ተግባር ውስጥ ጎፋ ነፍሱን ሰጥቶም ቢሆን ለወገኑ ሕይወት መትረፍ ይተጋል ።
ከሰሞኑ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌም የሆነው ይህ ነው ። ሰዎችን ከአደጋ ለማዳን " አሎ " ሲባል ሰምተው " አለሁ " ብለው የወጡ የዚህ ቀበሌና የአካባቢው ሰዎች ለሌላ አደጋ ተጋለጡ፤ ነፍሳቸውንም ሰጥተው ታሪክ አኖሩ ።
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም መላው የኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌና የአካባቢው ነዋሪዎችን በዚያ የሞት ላንቃ መካከል ለአንድ ዓላማ ያሰባሰበውም ይህ የይድረሱልኝ ጥሪ ነው ። በሰዓቱ እኒያ ደጋግ የኬንቾና አካባቢው ሰዎች በቀን 14 ምሽት ላይ ለሰዓታት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ " አሎ " ተባለ።
ከየአቅጣጫው ወደ ስፍራው የጎረፉ የኬንቾና አካባቢው ሰዎች ከአፈር ውስጥ የተቀበሩ፤ የቤት ፍራሽ በላያቸው ተጭኖ መውጫ ያጡ ወገኖቻቸውን ለመታደግ ነበር አእምሯቸውንም ሆነ አካላቸውን ያስገዙት ። እናም የአደጋው ሥፍራ መሬቱ ገና ያልረጋ ነበርና በመጀመሪያው አደጋ የተከፈተው የሞት ላንቃ ወገኖቻቸውን ለመታደግ የተሰበሰቡትን ሰዎች በዳግም አደጋ ዋጣቸው። በመጀመሪያው የመሬት መንሸራተት የአፈር ሲሳይ ከሆኑ ወገኖች በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ለወገን የመድረስ ቃል ኪዳን ሊያፀኑ ከየቤቱ የተመሙ ደጋግ ሰዎች ድንገት ተገምሶ በላያቸው ከወረደ አፈር ሥር እስትንፋሳቸው ተቋረጠ።
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ኃይለማርያም በቦታው ተገኝተው ተጎጂዎችን ያጽናኑ ሀዘኑንም የተጋሩ ሲሆን ክስተቱን ሲያስታውሱ "ዘግናኝ ቢሆንም ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም ሰውን ለማገዝና ለማዳን የሚከፈል መስዋዕትነት እስከምን ድረስ እንደሚወስድ የታየበት አጋጣሚ ነው” በማለት ነው የገለጹት።
“በጎፋዎች ዘንድ "አሎ" ከተባለ ከቤቱ የሚቀር ማንም የለም” ያሉት ደግሞ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ናቸው።
“ይህንን ጥሪ ሰምተው የወጡና ሰውን ለመታደግ ሲረባረቡ የነበሩ የኬንቾና አካባቢው ሰዎችን በሚዘገንን ሁኔታ አጥተናቸዋል” ብለዋል።
ኢንጂነር ዳግማዊ እንደተናገሩት፤ ወገኖቻቸውን ለማዳን ነፍሳቸውን አስይዘው ሲረባረቡ ከነበሩና የአፈር ሲሳይ ከሆኑ ሰዎች መካከል፣ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አቅመ ደካማ አባቶች ፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የፖሊስ አባላት ይገኙበታል ።
እነዚህን ለመታደግ ሲሉ ህይወታቸውን ያጡ፤ ሌላውን ለማዳን ህይወታቸውን የገበሩ ህጻን፣ ነፍሰ ጡር ሳይባል ከራስ ይልቅ ለሌላው መኖርን ያሳዩ መሆናቸው ሀዘኑን ከባድ ቢያደርገውም ደግሞ የጎፋዎች መገለጫ መሆኑ ያጽናናል። የዋና አስተዳዳሪው ስሜት ያሳብቃል። “የፖሊስ አመራር ፣ የፖሊስ አካላት እስከመጨረሻዋ ድረስ ሰዎችን ለማዳን እየሮጡ ራሳቸው ግን እዚሁ ቀርተዋል ፡፡ መምህራን ፣ የግብርና ባለሙያዎች በተመሳሳይ ህዝቡን ለማዳን እየሮጡ በዚሁ አደጋ ሰለባ ሆነዋል ፡፡ ሕፃናት ፣ ነፍሰጡር እናቶች ጭምር በዚሁ አደጋ ሰለባ ሆነዋል፡፡" በማለት ነው የገለጹት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት እንዳስታወቀው አደጋው በአጠቃላይ የ249 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል። በወቅቱ በተደረገው የነፍስ አድን ርብርብ 15 ሰዎችን በማትረፍ ህክምና እንዲያገኙም ተደርጓል ።
ማን ይናገር የነበረ …. እንዲል በዕለቱ ከሥፍራው ተገኝተው ነገር ግን በሌሎች እርዳታና በደቂቃዎች ልዪነት ውስጥ ባሉ አጋጣሚዎች ከሞት መንጋጋ ያመለጡ እማኞች እንደተናገሩት ሁሉም ሰዎች " አሎ "ን ሰምተው፤ የያዙትን ሁሉ ጥለው፤ አካፋና ዶማ አንጠልጥለው ሰው ለማዳን መምጣቸውን እንጂ አንዳች ድንገተኛ አደጋ መጥቶ ከዚያ ገደል ያስቀረናል ብለው በፍፁም አላሰቡም ። እናም እናት ጨቅላ ልጇ ላይ በር ዘግታ፤ አርሶ አደሩ ከብቶቹን ከበረት ትቶ፣ የህክምና ባለሙያው ተቋሙን ክፍት አድርጎ፤ የፖሊስ አባላት ከየተመደቡበት ቀጣና ተጠራርተው፤ አዳጊ ልጆች ወላጆቻቸውን ተከትለው ለይድረሱልኝ ጥሪው ምላሽ ለመስጠት ተጣደፉ እንጂ እንዲያ የተቻኮሉ እግሮቻቸው ከጭቃው ባህር ውስጥ ሰጥመው ይቀራሉ ብሎ የጠረጠረም የለ ።
"እኔና ባለቤቴ አራት ሕፃናት ልጆቻችንን በር ቆልፈንባቸው ወደ ስፍራው ሮጠን ነበር" ያሉት ወይዘሮ መክበቤ ኢያሱ፤ የእርጥቡ አፈር ክምር ባለቤታቸውን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላትን ውጦ ሲያስቀር እርሳቸው በደቂቃዎች ልዪነት በተፈጠረ አጋጣሚ መትረፋቸውን ነው የገለጹት። በወቅቱ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አራት ልጆቻቸው ላይ በር ዘግተው ድረሱልን ወደተባለበት በፍጥነት ያመሩት ወይዘሮ መክበቤ የተረፉበትን አጋጣሚ ሲገልፁ "በመሃል የልጆቼን ሁኔታ ተመልክቼ እስክመጣ ባለቤቴን ጨምሮ አምስቱንም አፈር ውጧቸው ጠበቀኝ" ብለዋል።
ሌላው ባለታሪክ ወጣት ኢዮብ ባሌ ደግሞ "በመጀመሪያው ዙር የመሬት መንሸራተት የተጎዱ የሁለት ቤተሰብ አባላትን ለማዳን ሁላችንም ደንግጠን ነበር ወደ ቦታው የሮጥነው" ብሏል ።
እርሱና ጓደኞቹ የይድረሱልኝ ጥሪውን እንደሰሙ በድንጋጤ ውስጥ ሆነው ወደ ሥፍራው እንደሄዱ የተናገረው ወጣት ኢዮብ፤ ከስፍራው ዘወር ብሎ ጫማውን አውልቆ፣ ልብሱን ቀይሮ ለቁፋሮ ራሱን እያዘጋጀ ባለበት ሰዓት ዳግመኛ የተናደው የመሬት ጉማጅ ወላጅ አባቱን፣ ታላቅ እህቱንና የአጎቱን ልጅ አፍኖ እንዳስቀራቸው ተናግሯል ።
የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ ደግሞ በመጀመሪያው አደጋ ምክንያት የሰሙትን የይድረሱልን ጥሪ ተከትሎ አሥር የፖሊስ አባላትን ይዘው ወደ ሥፍራው በፍጥነት አቅንተዋል።
ከስፍራው ከደረሱ በኋላም በአንድ በኩል በመጀመሪያው አደጋ ካፈሩ ውስጥ የተቀበሩ የሰዎችና እርዳታ የሚሹ ወገኖቻቸውን ለመታደግ ሲያስተባብሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቦታው ከዳግም ሥጋት የነፃ ባለመሆኑ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት የተሰበሰበውን ህዝብ እያስጠነቀቁ ነበር ።
የኬንቾና የአካባቢው ሰዎች ሰዎችን ለማዳን እየታተሩ ባለበት ወቅት አደጋው ዳግም ተከሰተ። ድንገት ከተፈጥሯዊ አቀማመጡ ተነጥሎ በመደርመስ እንደ ደራሽ ጎርፍ የተንደረደረው ጭቃነት ያለው የአፈር ክምር አጥለቀለቃቸው።
"እኔም በሰዎች እገዛና በፈጣሪ ቸርነት ነው የተረፍኩት" ያሉት ኢንስፔክተር በዛብህ፤ ይዘዋቸው ከመጡት የፖሊስ አባላት ሁለቱ ሕወታቸውን ሲያጡ አያሌ ወጣቶች፣ ሕፃናት፣ ወላጆችና በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ ልበ ቀናዎች ውድ ነፍሳቸውን ከፍለው ሰው መሆን እስከምን ድረስ እንደሆነ አስመሰከሩ።
በዚህ መልኩ የበርካታ ሕይወት የቀጠፈው አሰቃቂው አደጋ ድፍን ኬንቾን በዋይታ እንድትሞላ፤ አንዳንድ መንደሮች ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በየአንዳንዱ ቤት የሞት መርዶ እንዲሰማ አድርጓል ። ከቤት እንዳይወጡ አስጠንቅቀው በር ቆልፈውባቸው ወደ ይድረሱልኝ ጥሪ የሄዱ ወላጆቻቸውን ሲጠባበቁ የዋሉ ልጆች ይህን መቋቋም በማይችል አእምሯቸው አስከሬን ለመቀበል ተገደዋል ።
እናት በሆዷ እስከተሸከመችው ልጇ ከጭቃው ውስጥ አሸልባለች ። ሙሉ ቤተሰብ ሰው ለማዳን ከገደሉ ወርዶ አንዳቸውም በሕይወት ሳይመለሱ መቅውረታቸውም አስከፊው ክስተት ነበር። እናቶች ካፈር ውስጥ ተቀብረው የቀሩ ልጆቻቸው አስከሬን ተቆፍሮ እስኪወጣ እህል ባፋቸው ሳይቀምሱ ለቀናት ጠብቀዋል።
ናዳው ማንን ወዴት እንደቀበረ አይታወቅምና የተቆለለውን አፈር ጭረው እየዘገኑ በማሽተት የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን የሚፈልጉ ሀዘንተኞች ልባቸው እየደማ ጉልበታቸው እየዛለ ከአፈሩ ጋር ሲታገሉ ማየት ያማል። አስከሬን የተገኘላቸው ቤተ ዘመዶች ልባቸው በሀዘን ተሰብሮ በእንባ የታጀበ እልልታ ሲያሰሙ መመልከት ይከብዳል።
በዚህም ጎፋ ብቻ ሳይሆን ድፍን ኢትዮጵያ አዝናለች ። “ጎፋ ታሳ ፤ ኬንቾ ጎዝዲ ሻቻ ታሳ፤ ታና ሞ ታና ሞ፤ ጦሲ ዳንዳያ ኢሞ ” ብላለች። ኢትዮጵያ ለሶስት ቀን የሚቆይ የሀዘን ቀን አውጃ ሰንደቅ ዓላማዋ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጋለች ። ይህም ከአደጋው ባሻገር ዘመናትን የተሻገረ የጸና ሀገራዊ አብሮነትና አንድነት ለዓለም ያሳየ ነው ።
ነገር ግን ከመሪሩ ሀዘን በስተጀርባ ጎፋዎች ለ"አሎ" የሚሰጡት ቦታ ጥንትም እንደነበረው አሁንም መቀጠሉን ገልጠው አሳይተዋል። ሰውን ለማዳን የሰው ልጅ እስከ ምን ድረስ መዝለቅ እንደሚችል ያለስስት ነፍሳቸውን ሰጥተው በደማቁ ታሪክ ፅፈዋል። ከአደጋው ክስተት ጀምሮ፣ በነፍስ አድን ሥራ፣ በአስከሬን ፍለጋ፣ ሀዘንተኞችን በማፅናናትና ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ የተረባረቡ ኢትዮጵያዊያንን የተመለከተ ደግሞ የኬንቾና አካባቢው ሰዎች የፃፉት የአለኝታነት ታሪክ ተተርኮ የሚቆም ሳይሆን ነገም የሚቀጥል የኢትዮጵያዊነት መርህ መሆኑን ይገነዘባል።
የሰብዐዊ ፍጥረት የሕወት ዑደት ነውና ዛሬ በሀዘን የጎበጠችው ኬንቾ ከሀዘኗ ትፅናናለች፣ ኢትዮጵያም የእንቁ ልጆቿ ደግነትና ርህራሄ ማሳያ አድርጋ ክስተቱን ትዘክራዋለች።