ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በስካይ ላይት ሆቴል ስር ለማስተዳደር የተረከባቸውን ሎጅና ሪዞርቶች በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ስራ ያስገባል- አቶ መስፍን ጣሳው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ተገንብተው በስካይ ላይት ሆቴል ስር ለማስተዳደር የተረከባቸውን ሎጅና ሪዞርቶች በጥቂት ሳምንታት ወደ ስራ እንደሚያስገባቸው የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው  ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው የሚያደርግ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

በስምምነቱ መሰረትም አየር መንገዱ የሀላላ ኬላ ሪዞርት፣ የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም፣ እንዲሁም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን ተረክቧል፡፡

ስምምነቱም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የቱሪዝም ልማትን ለማስፋፋት የሚያግዝ ሲሆን አየር መንገዱም ይህን ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት አየር መንገዱ የተረከባቸውን ሎጅና ሪዞርቶቹን በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስታንዳርድ መሰረት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን በመረከብ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በሚመጡት ጥቂት ሳምንታት ደግሞ የቀሩት ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ባሻገር የሀገር ውስጥ ትስስርን ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ሚናው የጎላ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

መንግስት የቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ረገድ እያከናወነ ያለው ስራም አየር መንገዱ በቱሪዝም ልማት ላይ የበኩሉን ሚና እንዲጫዎት አድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም አየር መንገዱ የአውሮፕላን ማረፊያ በሌላቸው የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በመሬትና በውሃ ላይ የሚያርፉ አነስተኛ የቱሪስት ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም