በክልሉ ያልተገባ ዋጋ በጨመሩና ምርት በደበቁ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያልተገባ ዋጋ በጨመሩና ምርት በደበቁ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ
ነሐሴ 5/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ዋጋ የጨመሩና ምርት ደብቀው የተገኙ ከ990 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም በተለይ የሸቀጦች ዋጋን በመጨመርና ምርቶችን በመደበቅ በግብይት ሥርአቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተደራጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
ግብረ ኃይሉ ከ200 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል።
በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ዋጋ በጨመሩና ምርት አከማችተው በተገኙ ከ990 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የቃል፣ የጽሁፍና የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ነጋዴዎቹም ከ700 ሺህ ብር በላይ ቅጣት እንደተቀጡም አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የግብርና፣ የኢንዱስትሪም ሆነ የሌሎች ምርቶች እጥረት አለመኖሩን የተናገሩት ኃላፊው፣ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ በቀጣይም ይቀጥላል ብለዋል።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐቢብ አብደላ በከተማው ግብይት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን ለማረም የዋጋ ዝርዝር የመለጠፍና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሄም ሆኖ እህል በመደበቅና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የግብይት ስርዓቱ እንዲስተጓጎል ለማድረግ በሞከሩ 10 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግና የማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማው የተረጋጋ የግብይት ሂደት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ሐቢብ፣ ምርቶችን በኅብረት ሥራ ማህበራትና በሰንበት ገበያ አማካኝነት ለሸማቹ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቡታጅራ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ የተሰማሩት አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው በሰሞኑ በገበያው የተስተዋለው መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ እየተስካከለ መምጣቱን ተናግረዋል።
እርሳቸውም ለሸቀጦች በተተመነው የዋጋ ዝርዝር መሠረት እየሸጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በንግድ ሥራቸው ሕዝብ ላይ ዋጋ ጨምሮ ከማስጨነቅ ይልቅ አብሮነትን በማስቀደም እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምርቶችና ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ መስራታቸው አዳዲስ ደንበኛ ለማግኘት ዕድል እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ በቡታጅራ ከተማ የአገልግል የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐሪ መንግሥቱ ናቸው።
ሰርተን ሀብት የምንናገኘው ከኅብረተሰቡ እስከሆነ ድረስ ሀገራዊ ጉዳዮች ሲኖሩ በሰከነ መንገድ በማሰብ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።