የገጠሩ ነዋሪ በቴሌኮም ፕሮጀክቶች መካተቱና ተጠቃሚ መሆኑ ያስደስታል- የድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የገጠሩ ነዋሪ በቴሌኮም ፕሮጀክቶች መካተቱና ተጠቃሚ መሆኑ ያስደስታል- የድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች
ድሬዳዋ ፤ነሐሴ 05/2016 (ኢዜአ)፦ የዘመናዊ ኔትዎርክ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆናቸው የጀመሩትን ከድህነት የመላቀቅ ዘመቻ ለማሳካት እንደሚያግዛቸው የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
ኢትዮ ቴሌኮም ትናንት በድሬዳዋ አስተዳደር ዋሂል ክላስተር ኡሉል ሞጆ ቀበሌ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የሞባይል ኔትወርክ ታውር መርቆ አገልግሎት አስጀምሯል።
የዋሂል ገጠር ክላስተር አመራር አባላትና የኡሉል ሞጆ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም የዓመታት የሞባይል ኔትወርክ ጥያቄያቸውን በመፍታቱ ተደስተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የኡሉል ሞጆ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ረመቲ ሁሴን እንደገለጹት፤ መንግስት የዓመታት የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት ጥያቄያቸውን በመፍታቱ ተደስተናል ብለዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ የቀበሌው አርሶ አደር በውጭ አገራት ካሉ ዘመዶቹ የሚላክለትን ገንዘብ በቀላሉ ለመቀበል እና ወደ ከተማ ለትምህርት ከላካቸው ልጆቹ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እንደሚያስችለው ገልፀዋል።
"የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎቱ ዘመናዊ እና ቀለል ያለ ህይወት ለመምራት ያግዘናል" ሲሉም ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የሞባይል ኔትወርክ ፍለጋ ብዙ ኪሎሜትር መንገድ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር የገለፀው ደግሞ ወጣት መሐመድ ኢብራሂም ነው።
ወጣት መሐመድ እንደገለፀው፤ የሞባይል ኔትወርክ ታዎር በክላስተሩ መተከሉ በቴሌ ብር አማካኝነት ማንኛውንም አገልገሎቶች በመጠቀም እንደ ከተማው ህዝብ የዲጂታል ዘመን ሰው ሆነናል" ብለዋል።
በስነስርዓቱ ላይ የአካባቢው የኃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች የተዘረጋላቸውን የኔትወርክ ታዎር እንደ ብሌናቸው በመጠበቅ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የክላስተሩ አስተዳዳሪ አቶ አብዲ ኑር እንደገለፁት፤ የክላስተሩ አርሶ አደር ማህበረሰብ የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ከሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆናቸው የጀመሩትን ከድህነት የመላቀቅ ጉዞ ለማሳካት ያግዛል።
የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣቶችና ሴቶች የስማርት ሞባይል ባለቤት በመሆናቸው ከገበያው ጋር ለመተሳሰር እና ከምርቶቹ ተገቢውን ጥቅም ተደራድረው ለማግኘት ያስችላቸዋል ሲሉም አክለዋል።
በዋሂል ገጠር ክላስተር በኡሉል ሞጆ ቀበሌ የተገነባውን የሞባይል ኔትወርክ ፕሮጀክቱን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኢትዮ ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ጣሰው ሽመልስ፣ የኢትዮ ቴሌኮም 'ቺፍ ከስተመር ሰርቪስ ኦፊሰር' አቶ ተሬሳ በለጠ እና የዋሂል ገጠር ክላስር ከፍተኛ የአመራር አባላት ናቸው።