ቀጥታ፡

በሴቶች ማራቶን ፍጻሜ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለድል ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች ማራቶን ፍጻሜ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ አትሌት አማኔ በሪሶና አትሌት መገርቱ ዓለሙ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

አትሌት ትዕግስት በኦሊምፒክ ስትሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ800 ሜትር ማጣሪያ ተሳትፋ ነበር።

እ.አ.አ በ2023 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ሰብራለች።

አትሌቷ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌይ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በ2 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ አሻሽላለች።

በማራቶን ከ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ በታች የገባች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትም ሆናለች።

ትዕግስት ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ ናት።

በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን የምታደርገው አትሌት አማኔ በሪሶ እ.አ.አ በ2022 በቫሌንሺያ ማራቶን 2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በወቅቱ የገባችበት ጊዜ በሴቶች ማራቶን የዓለም አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።

አማኔ እ.አ.አ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች።

አትሌት መገርቱ ዓለሙ እንደ አማኔ ሁሉ በፓሪስ የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።

መገርቱ እ.አ.አ በ2022 በለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ32 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በቶኪዮ እ.አ.አ በ2020 በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሴቶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ኬንያዊቷ አትሌት ፔሬዝ ጄፕቺርቺር እና 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ሁለተኛ ፈጣን ያላት በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ 1 የወርቅ እና 2 የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 48ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በፓሪስ ሲካሄድ የቆየው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም