በአዲስ አበባ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢን ለማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢን ለማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ገቢን ለማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መደረጉ ተመላከተ።
ከተማ አስተዳደሩ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንግሥት ሥራ አፈፃጸም ግምገማና የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ ዝግጅት በዓድዋ መታሰቢያ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘገየ በላይነህ በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 151 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ ታቅዶ 147 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የተገኘው ገቢ የዕቅዱን 97 በመቶ መፈጸም መቻሉን ጠቅሰው ይህም የታክሰ አሰባሰብ ሂደት ላይ ያሉ አሰራሮችን በማዘመንና አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ባለፈው በጀት ዓመት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከርና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም 2017 በጀት ዓመት ከ230 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ቀልጣፋና ፈጣን የሆነ የግብር አሰባሰበ ሥርዓት ገቢራዊ በማድረግና ብቁ የሰው ኃይልን ከቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት።
የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲሳካ ገቢን በማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የገለጹት ኃላፊው ማሻሻያው ለግብር ከፋዩም ለመንግሥትም ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ታክስ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለውን ምጣኔን ማሻሻል እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ የወጪ ንግድ አቅምን ማጎልበት የሪፎርሙ ትኩረት መሆኑን ጠቁመዋል።
በከንቲባ ጽህፈት ቤት የአቤቱታና ቅሬታ ዘርፍ ኃላፊ አባይነህ አመርጎ በበኩላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ለማቅረብ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል በተለይም አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም ሌብነትና ብልሹ አሰርርን ለማስቀረት ተጠያቂነት የሚያስፍን የአሰራር ሥርዓትን የማጠናከር ተግባርም እንደሚሰራ ጠቁመው በዚህም ኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።