በጌዴኦ ዞን የአንድ ሺህ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን የአንድ ሺህ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀመረ
ዲላ ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድ ሺህ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዛሬ በዲላ ዙሪያ ወረዳ ተጀምሯል ።
የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ በወረዳው ስሶታ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበርካቶችን ሕይወት የቀየረና የመረዳዳት እሴትን በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው።
በዞኑ የሚካሄደው ለአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም የዚሁ አካል መሆኑን ገልፀዋል።
የዞኑ አስተዳደር የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ነዋሪዎቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የልማት ዘርፎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታው የዞኑ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ግለሰቦችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግነት ኃይሉ ናቸው።
በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከማገዝ በተጨማሪ፤ የኅብረተሰቡን የመተጋገዝና የመደጋገፍ እሴት በይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች በቂ የግብዓትና የሰው ኃይል በማዘጋጀት የቤቶቹ ግንባታን በማፋጠን በአጭር ጊዜ ለአገልግሎት ለማብቃት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የመኖሪያ ቤት ከሚገነባላቸው ወገኖች መካከል በዲላ ዙሪያ ወረዳ ስሶታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ደያሳ መኖሪያ ቤታቸውን ለመገንባት ግብዓቶች ተሟልተው በማየታቸው የተለየ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ከመኖሪያ ቤት ጋር ተያይዞ ይገጥማቸው የነበረን ችግር እንደሚቀርፍላቸውም ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀው ሌሎች የእርሳቸውን ቤት ለመገንባት ሲረባረቡ በማየታቸው በቀጣይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሰማራት መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል።
''በጎነት ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በመሆኑ መጠናከር አለበት'' ያሉት ደግሞ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቤት ግንባታው ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ቄስ ወልዴ አየለ ናቸው።
በበጎነት ለወገን መድረስ ከሚፈጥረው የመንፈስ እርካታ በተጨማሪ አንድነታችንንና ፍቅራችንን የምንገልጽበት መንገድ በመሆኑ ከሚተርፈን ሳይሆን፤ ካለን አካፍለን ለወገኖቻችን በጎ መዋል ይጠበቅብናል ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ እንደምታጠናክር ገልፀው ሌሎችም በየአካባቢያቸው መሰል መልካም ተግባራትን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።