ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ከቡና ወጪ ንግድ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ብቻ ወደ ውጭ ሀገራት ከላከችው ቡና 185 ነጥብ 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ54 ነጥብ 29 ሚሊዮን ዶላር (43 በመቶ) እንደሚበልጥ አመልክቷል።

ገቢው የተገኘው ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላከው 40 ሺህ 531 ቶን ቡና ነው።

የተላከውም መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ17 ሺህ 758 ቶን ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።


 

ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 298 ሺህ 500 ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ መገለጹ ይታወሳል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 65 ሀገራት ቡና መላኩ ተጠቁሟል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ቤልጂየም፣ጀርመን፣ቻይና፣ ጃፓንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላከችባቸው ሀገራት መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱንም ነው ባለስልጣኑ የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም