ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በመጪው ሰኞ ይጀመራል

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ) -በድሬዳዋ ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ  ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰቡ ሂደት እንደሚጀመር የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር  መሐሙድ ድሪር ገለፁ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በመጪው ሰኞ በሚጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በመላው አገሪቱ በህዝብ  ከተመለመሉ ተወካዮች አካታች፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለአገራዊው ምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን ማሰባሰብ ጀምሯል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከጋምቤላ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለአገራዊው ምክክር የሚበጁ አጀንዳዎች ተሰብስበው መጠናቀቃቸውን አስታውሰዋል።

በሐረሪ ክልል አጀንዳ የማሰባሰቡ የምክክር ሂደት ዛሬ መጀመሩን ገልፀው በድሬዳዋ አስተዳደር ደግሞ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ  እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክሩ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የወረዳ የህዝብ ተወካዮች፣ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች  እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉም አስረድተዋል።

እነዚህ ተሳታፊዎች በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በእኩልነት ለአገራዊ መግባባት ይጠቅማሉ የሚሏቸውን መሠረታዊ ሃሳቦችን  እንደሚያቀርቡ ነው የገለፁት።

በመሆኑም በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ለውይይቱ መሳካት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም