ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ሁለንተናዊ ተሳትፎን ያጎለብታል-ተሳታፊዎች

ሐረር፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፡- አገራዊ ምክክሩ ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት ድርሻው የጎላ በመሆኑ ለስኬታማነቱ እንደሚሰሩ በሐረሪ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ላይ የተሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተመራጮች እና ከባለድርሻ አካላት አጀንዳ የሚያሰባስብበትን መድረክ እያካሄደ ነው።

ተወካዮቹ ኮሚሽኑ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ለአገር ሰላምና ልማት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለስኬታማነቱም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በዕድሮች ተወክለው በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አቶ በትረ ወልደ ማርያም እንደገለፁት፤ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን አለመግባባትንና ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ከተወካዮች መረጣ ጀምሮ በንቃት በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።


 

ምክክሩ ለመጪው ትውልድ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ ለምክክሩ ስኬታማነት  እየሰራሁ ነው ብለዋል።

"ሌላ አገር የለንም አንድ ኢትዮጵያ ነች አገራችን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት እድል ስላገኘን ፈጣሪን ልናመሰግን ይገባል"  ያሉት የሃይማኖት ተቋማትን ወክለው በመድረኩ የተሳተፉት አቶ መሐመድ ሐሰን ናቸው።


 

ምክክሩም የአገሪቱን አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን እድል መጠቀምና ተሳትፏችንን ማጎልበት ይገባናል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

መላዕከ ኃይል አባ ኪዳነማርያም በበኩላቸው የምክክር ሂደቱ ሁሉንም አሳታፊ ማድረጉ ለስኬታማነቱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፣ በመድረኩ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

''የምክክር መድረኩ የጋራ አስተሳሰብ እንዲጎለብት የሚያደርግና የአገሪቱን ችግሮች በምክክር ለመፍታት ጠቃሚ በመሆኑ ተሳትፎዬን አጠናክራለሁ'' ብለዋል።

ኮሚሽኑ በሃገር ሰላም አንድነትና ልማት ላይ በጋራ እንድንሰራ ያመቻቸውን መድረክ ወደ ዕድል ቀይሮ ሃገራዊ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ያሉት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው የተሳተፉት ወይዘሮ ፈርዶሳ አቡበከር ናቸው።


 

ምክክሩ እንደ ሃገር የሚፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል፣ የአገሪቱን እድገት የሚያስቀጥልና ትውልድ በአገሩ እንዲኮራ የሚያደርግ በመሆኑ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ እንደተናገሩት፤ ተሳታፊዎች መከባበርና መደማመጥን መሰረት ባደረገ  መልኩ ተነጋግረው አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።


 

''የምክክር ባህልን በሂደት በመገንባት፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ተስፋ በማለምለም ግጭቶችና አለመግባባቶች በጦርነት አማራጭ ሳይሆን፤ በውይይትና በምክክር የመፍታት ልምድ እናሳድጋለን'' ሲሉም ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣  የተለያዩ ተቋማት ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ሌሎች አካላት ተወያይተው፣ የአጀንዳ ሃሳባቸውን እንደሚያዘጋጁ እና እንደሚያቀርቡም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም