የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን ዕድገት በተሟላ መንገድ ማስቀጠልን ማዕከል ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን ዕድገት በተሟላ መንገድ ማስቀጠልን ማዕከል ያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን ዕድገት በተሟላ መንገድ ማስቀጠልን ማዕከል ያደረገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፥ በወቅታዊ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ እና የክረምት ወቅት የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በዓመቱ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የልማት ዕቅዶች መነሻነት ለትውልድ የሚሻገሩ የልማት ስራዎችን የሰራችበት የስኬት ዘመን ነበር ብለዋል።
ለአብነትም ለኢኮኖሚ ዕድገት አዳዲስ ብስራት የሆኑ የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም እና ሌሎች የልማት መስኮች ስኬታማ ስራ የተሰራበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጣዊና እና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን በመቋቋም ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ አይበገሬነቱን ያስቀጠለበት ዓመት ነው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ኢትዮጵያ እያስመዘገበች የምትገኘውን ዕድገት በማጽናት በተሟላ መንገድ ማስቀጠልን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ዕድገትን ለማስፈን በማስፈለጉም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል።
ማሻሻያው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ የተሻለ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር፣ የዘርፎች ምርታማነትና ጠንካራ የመንግስት የማስፈጸም አቅም መፍጠርን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።
ፖሊሲው በአምራች ኢንዱስትሪው፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና ሌሎች መስኮች ዕድገትን በማስቀጠል የፋይናንስ መረጋጋትን፣ የፕሮጀክት ውጤታማነትንና የመንግስትን ገቢ ማሻሻልን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ለማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ስኬት ኢትዮጵያዊያን በልማት መስኮችና ተያያዥ ጉዳዮች የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ሚና መወጣት እንደሚኖርባቸው ጠይቀዋል።
አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆም በአቋራጭ ለመበልጸግ ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ምርትን በመደበቅና ዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
መንግስት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የተደረገው ማሻሻያ ለንግዱ ማህበረሰብ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስትም የምርት እንቅስቅሴን የሚገድቡ ጉዳዮችን መፍትሔ እየሰጠ ይሄዳል ብለዋል።
የከተማና የክልል መስተዳድሮችም ምርቶች በሁሉም አቅጣጫ በተሳለጠ መልኩ እንዲሰራጩ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም ድረስ 1ኛውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በዓድዋ የድል መታሰቢያ ሙዚየም እንደምታስተናግድ አስታውቀዋል።
"ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ፎረም የአህጉሪቱን ከተሞች ቁልፍ ጉዳዮች ለማሳለጥ የሚያገለግል ነው ብለዋል።
የመኸር ወቅት የልማት ስራን በተመለከተም 20 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን በተያዘው ዕቅድ መሰረት እስካሁን 18 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬት በሰብል ተሸፍኗል ብለዋል።
በክረምቱ ለግብርና ልማት ስራ አመቺ ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም ዜጎች በመሬት መንሸራተትና እና በጎርፍ ሙላት ሊደርስ ከሚችል አደጋ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብን ለማሳካት በሁሉም አካባቢዎች መርሐግብሩ እየተከናወነ ነው ብለዋል።