በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ ግብይት ሲያካሄዱ በተገኙ 178 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ ግብይት ሲያካሄዱ በተገኙ 178 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 4 /2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ ግብይት ባካሄዱና ምርት ሰውረው በተገኙ 178 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከ45 ሺህ 300 ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ወደ ክልሉ እንዲገባ መደረጉንም ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አምቢሳ ያደታ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በንግድ ድርጅቶቹ ላይ እርምጃ የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመጨመርና ምርት በመሰወር ተግባር ተደርሶባቸው ነው።
ቢሮው ድርጊቱን ፈፅመው ባገኛቸው 85 የንግድ ድርጅቶች የማሸግ፣ በ93 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ የማስጠንቀቂያ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በፍጆታ ምርቶች ላይ እየተካሄደ ያለውን ህገ ወጥ ግብይትና የምርት ስወራ ለመከላከል በክልል ደረጃ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የክትትልና ቁጥጥር ሰራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ የቢሮው ኃላፊ ገልጸዋል።
ግብረ ኃይሉ በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎችም ህገ -ወጥ ግብይቱንና የምርት ስወራን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ ከ45 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ጋምቤላ ከተማና በማጃንግ ዞን እንዲገባ መደረጉን አቶ አምቢሳ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ከ695 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት ወደ ክልሉ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።