ቀጥታ፡

የፅናትና የስኬት ተምሳሌቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክ አዲስ ታሪክ ፅፏል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ታሪክ የተወዳደረ በእድሜ ትልቁ አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርቷል።

በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወንዶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር ዛሬ ከቀትር በፊት ተካሄዷል።

በዚሁ ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን በማሻሻል ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

አትሌት ደሬሳ ገለታ አምስተኛ ወጥቷል።

አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ 39ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።

አትሌት ቀነኒሳ በ42 ዓመቱ በመሮጥ በኢትዮጵያ የ15 የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በውድድሩ ላይ የተሳተፈ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርቷል።

ቀነኒሳ በ4 የኦሊምፒክ ተሳትፎው 3 የወርቅና 1 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ለኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ በርካታ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

በስኬትና በድል የታጀበ የአትሌቲክስ ሕይወት ያለው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2004 በግሪክ አቴንስ በተካሄደው 28ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ነበር።

ቀነኒሳ በውድድሩ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

በቻይና ቤጂንግ እ.አ.አ በ2008 በተካሄደው 29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ አትሌቱ በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ለሀገሩ አኩሪ ታሪክ ሰርቷል።

ቀነኒሳ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት ያስመዘገበው ጊዜ እድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ አትሌት በማራቶን ያስመዘገበው የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓት በሚል ተመዝግቦለታል።

የአሜሪካው የስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ 'ኢኤስፒኤን' በቅርቡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን 10 ታላላቅ አፍሪካውያን ስፖርተኞችን ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን አካቶታል።

ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ኦሊምፒክ መድረክ መድረክ የተመለሰው አትሌት ቀነኒሳ በዛሬው ውድድር ባያሸንፍም የኢትዮጵያውያንን ልብ ባሳየው ብርታትና ፅናት አሸንፏል።

እድሜ ሳይበግረው በአስቸጋሪው የፈረንሳይ አየር ንብረት ውድድሩን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም