የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የኒዩሮሳይንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የአዕምሮና ነርቭ ህክምናን ከአንጎልና ሕብለሰረሰር ቀዶ ሕክምናን ጋር በማቀናጀት የኒዩሮሳይንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ሁሉን አቀፍ ህክምና አገልግሎት ለተገልጋዮች እየሰጠ ይገኛል።

አሁን ላይ ደግሞ ወደ ተለያዩ አገራት በመሄድ መታከምን የሚያስቀሩ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን  ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። 

በዚህም ሆስፒታሉ የአዕምሮና ነርቭ ህክምናን ከአንጎልና ሕብለሰረሰር ቀዶ ሕክምናን በማቀናጀት የኒዩሮሳይንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።


 

ማዕከሉ የጥናትና የምርምር እንዲሁም የህክምና አገልግሎት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ለማዘመን ከጤና ሚኒስቴርና ከዓለም ባንክ ድጋፍ በቅርቡ የሚጠናቀቅ እድሳት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ሆስፒታሉ የአዕምሮንና የነርቭ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአንጎል ቀዶ ህክምና አገልግሎት መጀመሩን አስረድተዋል።

ሦስቱን ህክምናዎች ከድንገተኛና ጥብቅ የህክምና ክብካቤ ክፍል (ICU) አገልግሎት እንዲሁም ከተሃድሶ ህክምና ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ለያዘው ዓላማ የሚያግዙ 26 የሕክምና ባለሙያዎች መቀጠራቸውንና በዘርፉ ዓለምን ከሚመሩ የኒዩሮሳይንስ የልህቀት ማዕከላት ጋር ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መገርሳ ዓለሙ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የኒዩሮሳይንስ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የሚያግዙ የተለያዩ ሰነዶች ዝግጅት መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።  


 

ከዚህ በተጨማሪምሆስፒታሉ ዓላማውን ለማሳካት በዘርፉ በቂ የሕክምና ባለሙያዎች እንዳሉትና  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋርም ጠንካራ ትብብር መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።  

የልህቀት ማዕከሉ ዋነኛ የሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን የስትሮክ ህመም ጨምሮ ሌሎች መሰል በሽታዎችን በማከም ለህሙማን መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም